ሲሳይ ኃይሉ ጩፍሬ የተባለው ተከሳሽ ካልተያዙ ሁለት ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7፡20 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጀሞ ኪሩ ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው የግል ተበዳይ የራይድ አገልግሎት የሚሰጥበትን 1 ሚሊዮን 400 ሺ ብር የሚገመተውን ቪትዝ መኪና ይዞ ቆሞ እያለ ተከሳሽ ወደ እርሱ በመምጣት ፒያሳ እንዲያደርሳቸው በመጠየቅ 600 ብር ይስማማሉ፡፡
በዚሁ መሠረትም ተከሳሽ ከመኪናው የኋላ ወንበር በሾፌሩ በኩል፣ አንደኛው ያልተያዘው ግብረ-አበር ጋቢና፣ 2ኛና ያልተያዘው ግብረ-አበር ደግሞ በተሳፋሪ በኩል ከኋላ ወንበር በመቀመጥ በመጓዝ ላይ እንዳሉ ልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 08 አለም ሰላም ድልድይ አካባቢ ሲደርሱ ጋቢና የተቀመጠው ታማሚ በመምሰል ሊያስታውከኝ ነው መኪናውን አቁምልኝ ሲል የግል ተበዳይ ዳገቱን ጨርሼ ላቁምልህ በማለት በፍጥነት ሲያሽከረክር ተከሳሽ የግል ተበዳይን በእጁ አንገቱን አንቆ በመያዝ እና በሁለት በኩል ስለት ያለውን ጩቤ አንገቱ ላይ አድርጎበት በማስፈራራትና ሁለቱንም እጆቹን በስለት በመውጋት ጉዳት እንዲደርስበት ያደረጋል፡፡
2ኛው ያልተያዘው ግብረ-አበር ደግሞ የግል ተበዳይን እንዳይከላከል ከኋላ ተበዳይን በመጎተት የመኪናውን የእጅ ፍሬን ስቦ ተሽከርካሪው እንዲቆም በማድረግ የግል ተበዳይን በጋራ በመተባበር ከተሽከርካሪው ውስጥ አውጥተው ጥለው መኪናውን የወሰዱ ሲሆን ተከሳሽ በፖሊስ ክትትል ከነተሽከርካሪው ይያዛል፡፡
በመሆኑም በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/1/ለ/ መሠረት ተከሳሽ በፈፀመው የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡