በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ያለአግባብ የሲሚንቶ ግዢ በመፈጸም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የአገልግሎቱ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ ክስ ያቀረበባቸው አራት ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 3ኛ ሙስና ወንጀል ችሎትም አራቱም ተከሳሾች በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን በመስጠት፣ የተከሳሾችን መከላከያ ለመስማት ለሚያዚያ 25 እና 26 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾች በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ውስጥ 1ኛ ተስፋዬ ደሜ በብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር፣ 2ኛ አሸናፊ ተስፋዬ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ሃላፊ፣ 3ኛ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ፣ ተገቢ ያልሆ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ወራት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስም ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊዬን 99 ሺ 360 ብር ጥቅም ያገኙ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በሥልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል በዐቃቤ ሕግ ክስ መመስረቱን አስመልክተን መዘገባችን ይታወሳል፡፡