በኢትዮጵያ ከካፒታል ገበያ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ተአማኒነት ግብረ-ኃይል በማቋቋም የትብብር እና ቅንጅት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ አዋጅ ጸድቆ የካፒታል ገበያ መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር፣ በግብይት ስርዓቱ ላይ ተአማኒነትንና ግልጽነትን ለማጎልበት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተቋቁሞ ወደ ስራ የገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በዚህ የካፒታል ገበያ ላይ የሚሳተፉ አካላት ሕግና ስርዓትን አክብረው ሊሰሩ እንደሚገባና የሕግ ጥሰት የሚፈጽሙ አካላት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
በስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ህጋዊና ከወንጀል ድርጊቶች የጸዳ ለማድረግ በተቋማቱ መካከል ቋሚና ቀልጣፋ ቅንጅታዊ የአሠራር ስርዓት መዘርጋት የካፒታል ገበያውን ተአማኒነት ለማረጋገጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡