ላለፉት 60 ዓመታት በስራ ላይ ቆይቶ ከወራቶች በፊት የተሻሻለው የንግድ ሕግ አቅፏቸው የነበሩትን ስለ ባንክ እና ኢንሹራንስ አገልግሎት የሚያወሩ ድንጋጌዎችን የሚተካ ሕግ ለማርቀቅ እና እራሱን የቻለ መድብል ሆኖ እንዲወጣ የሚያስችል የረቂቅ ስራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡
በዚህ የረቂቅ ማስጀመርያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እንደገለጹት ከዚህ በፊት ስራ ላይ በነበረው የ1952ቱ የንግድ ሕግ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያስችል ሕግን ከማርቀቅ እና እንዲጸድቅ እንዲሁም ለአተገባበር ምቹ ለማድረግ የተሰራውን ስራ አስታውሰው በህጉ ስለ ባንክ እና የኢንሹራንስ የሚደነግጉትን ድንጋጌዎች እንደ ሌሎች የህጉ ክፍሎች ሁሉ አሁን ያለንበት ወቅት ከሚፈልገው ዘመናዊ የባንክ እና ኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር አብሮ በሚሄድ መልኩ አሻሽሎ ወደ ስራ ማስገባቱ ተገቢ በመሆኑ ህጉን ለማሻሻል ያመች ዘንድ በዘርፉ በቂ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን አባላት ያቀፈ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ እንዲገባ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለስራው ጥራትና ውጤታማነት ሲባልም ከውጭ ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ የተውጣጡ አማካሪዎች እንዲካተቱ መደረጉን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ስራ ለመሥራት የተቋቋመው ቡድን ሙሉ ግዜውን ሰጥቶ የረቂቅ ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማከናወን ጥራቱን የጠበቀ እና ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሕግ እንዲወጣ ሙያዊ ሚናቸውን ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው ይህ የሚሆነው ግን ተቋማት በሙሉ ፍላጎት እና ሃሳብ ስራውን መደገፍ ሲችሉ እና የተጠየቁትን ዕገዛ ሁሉ ማበርከት ሲችሉ ነው ብለዋል፡፡
በመቀጠልም የባንክ እና የኢንሹራንስ ጉዳዮችን በውስጡ የሚይዘውን የፋይናንስ አገልግሎት መድብል ረቂቅ ሕግ ለማዘጋጀት የተነደፈው መነሻ ዕቅድ የቀረበ ሲሆን የቀረበውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ግብዐት ተሰባስቧል፡፡
በመጨረሻም ውይይቱን የመሩት ሚኒስትር ዴዔታው አቶ አለምአንተ አግደው ተሳታፊዎች ያነሳችኋቸው ሃሳቦች ዕቅዱን ለማዳበር እና የረቂቅ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚጠቅሙ በመሆኑ ለማካተት እንሞክራለን ካሉ በኋላ የረቂቅ ስራ በይፋ መጀመሩን ገልጸው ለረቂቅ ዝግጅት ቡድኑ አባላት የስራ አቅጣጫ በመስጠት የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡
በውይይት መድረኩ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከባንክ እና ኢንሹራንስ ማህበራት በግል ከሚሰሩ ጠበቆች እና የሕግ አማካሪዎች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአለም ባንክ እና ከፍትሕ ሚኒስቴር የተውጣጡ የስራ ሓላፊዎች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡