የፍትሕ ሚኒስቴር የ2017 የመጀመሪያ 100 ቀን የሪፎርም እና የዋና ዋና ኢኮኖሚ አፈፃፀም እና የተቋሙ የ1ኛ ሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሄደ

Ministry of Justice Holds Discussion on the 2017 First 100-Day Reform and Macroeconomic Performance, and the Institution's First Quarter Plan Implementation

የፍትሕ ሚኒስቴር የ2017 የመጀመሪያ ሀገራዊ የ100 ቀን የሪፎርም፣ የዋና ዋና ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አፈፃፀም እና የተቋሙ የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ጥቅምት 19 ቀን 2ዐ17 ዓ.ም የተቋሙ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት ውይይት አካሄዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ ከዚህ ቀደም በነበራቸው የስራ አጋጣሚ የፍትሕ ዘርፉን መሠረታዊ ሂደት ለማየት በጣም ብዙ እድሎች እንደነበሯቸው ገልጸው በቀጣይ በዚህ ተቋም የሚሰሩ ሰፊ ስራዎች እንዳሉ አውስተዋል፡፡ አያይዘውም በተቋሙ ውስጥ ያለን አካላት ስራችንን በአግባቡ፣ በታማኝነት እና በታታሪነት መስራታችን ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ አለው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ በቀጣይ የተቋም ግንባታ እና ዲጂታላይዜሽን ስራዎች ላይ ውሳኔ በማስተላለፍ ቀደም ብሎ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስራዎችን ዳር የማድረስ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በመቀጠልም የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የ2017 የመጀመሪያ 100 ቀን የሪፎርም እና የዋና ዋና ኢኮኖሚ አፈፃፀም ሪፖርቱን ሲያቀርቡ በአጠቃላይ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተው ሪፖርቱ እንደ ሀገር ምን ላይ እንዳለን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የ100 ቀን ሪፖርቱ በዋናነት ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አዝማሚያና ለኢትዮጵያ ያለው አንድምታ ምን እንደሆነ፣የሪፎርሙ ተጠባቂ ፋይዳዎች ምን እንደነበሩ፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም አፈጻጸም ውጤቶችና አዝማሚያዎች ምን እንደሚመስሉ እንዲሁም የዋና ዋና ፕሮጀክቶች አፈፃጸም ላይ ያተኮረው ነበር፡፡

የተቋሙ የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ደሳለኝ መንግስቴ አማካኝነት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ በዋናነትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማነትን ከማሳደግ አንጻር የተለያዩ የተቋሙን አሰራሮች ለመከታተል የሚያስችሉ የዲጅታላይዜሽን ስርዓት የሚያሳልጡ ስርዓቶች/Systems/ ለምተው አተገባበራቸውን በተመለከተ በተወሰኑት ላይ ሥልጠና ተሰጥቶ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘም የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በመሆን ለመሥራት የስራ ውል ስምምነት መፈረሙን የገለጹት ዳይሬክተሩ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣ የወጣት ጥፋተኞች መረጃና የጾታዊ ጥቃት አድራሾች የመረጃ ስርዓት (WCCRIMS) ለማበልጸግ ከአልሚው ተቋምና ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ዶክመንት መዘጋጀቱንም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል የበጎ አድራጎት ስራዎች አፈፃፀምን በተመለከተ በአንድ ጀንብር አረንጓዴ አሻራ በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ ክልል እና በአዳማ ከተማ በአጠቃላይ ወደ 25000 የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች የመትከል ስራ ከመከናወኑ ባሻገር ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የት/ት ቁሳቁስ፣ ለአቅመ ደካሞች አዲስ ቤት የመገንባት ስራ፣ እንዲሁም በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሲቪል ማህበራትን በማስተባበር ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁሶችና የምግቦች ድጋፍ መደረጉን እንዲሁም በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሃ-ግብር መካሄዱ በዚህ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የበጎ አድራጎት ተግባራት መሆናቸው በሪፖርቱ

ተመላክቷል፡፡

የመንግሥትና የሕዝብን ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በተመለከተ በአጠቃላይ 8,854 መዛግብት ሲሆኑ የገንዘብ መጠናቸውም ብር 14,918,590,544.42 የቀጥታ ክስ መዛግብት ላይ ክርክር ተደርጓል። በቀጥታ ክስ ክርክር ከተደረገባቸው መዛግብት መካከል 2,471 መዛግብት ላይ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ዐ/ሕግ የረታባቸው ጉዳዮች 2,273 መዛግብት ሲሆኑ አፈጻጸሙም 91.98% እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የወንጀል ምርመራ መዝገቦች አፈጻፀምን በተመለከተም እንዲሁ የፍትሕ ሚኒስቴር አጠቃላይ በዐ/ሕግ የነበሩ 18,282፣ ውሳኔ ያገኙ መዛግብት ብዛት 16,826፣ ወደሚቀጥለው የተዛወሩ 1,443 ሲሆን አፈፃፀሙ 92.1% ሲሆን፤

የወንጀል የክርክር መዝገቦችን አፈጻፀም በተመለከተ የክርክር መዝገቦች የመርታት ምጣኔ 98 በመቶ ለማድረስ በዕቅድ ተይዞ በፍትሕ ሚኒስቴር ክርክር የተደረገባቸው 20235፣ ውስጥ 3056 ውሳኔ ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጥፋተኛ የተባሉ መዛግብት 2,958 እንዲሁም በነፃ የተሰናበቱ መዛግብት ብዛት 98 በመሆኑ አፈፃፀሙ 98.8% እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በቀረቡት ሪፖርቶች ዙሪያ ተሳታፊዎች ላነሷቸው የተለያዩ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎች እና ሀሳቦች በበላይ አመራሩ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የእለቱ መድረክ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Legal Reform Performance Evaluation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች