የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽህፈት ቤት ከዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር በዓለማቀፉ በሰብዓዊነት ህግ ዙሪያ ከክልሎች ከተውጣጡ የፍትህና የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊዎች ጋር የስትራቴጂ ወርክሾፕ አካሔደ

Ministers’ Task Force Office Collaborates with International Red Cross to Conduct Strategic Workshop on International Humanitarian Law

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ከማጣራት፤ ተጎጂዎችን ከመጠበቅና ከመደገፍ አንጻር ስራዎችን ለማስተባበር የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽህፈት ቤት ከዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ዓለማቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ (international humanitarian law) እና የሰብዓዊ መብት ገዢ መርሆች በተቋማቱ አሰራሮች ውስጥ ደረጃ በደረጃ በዝርዝር በሚዘረጉብት ሁኔታ ላይ ከክልሎች የፍትሕ ቢሮዎች፣ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ እና የአስተዳደር እና የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ከሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የቆየ ወርክሾፕ በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ፡፡

መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጸጋ እንደተናገሩ ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የሕግ ማስከበር ስራው ከተጀመረ በኋላ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጥምር ምርምራ ያደረገ ሲሆን የምርመራው ግኝቶች ጥቅምት 2014 ዓ.ም ይፋ መደረጋቸውን አውስተዋል፡፡

መንግሥትም ብዙዎቹን ግኝቶች በአወንታዊ መልኩ የተቀበላቸው መሆኑን የተናገሩት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ በዚህ አግባብም ጉዳዩን የሚያጣራ በስሩ አራት ኮሚቴዎችን የያዘ የሚኒስትሮች ግብረኃይል በማቋቋም ወደስራ መግባቱን ለመድረኩ አብራርተዋል፡፡ የዚህ ሥልጠና ዋና ዓላማም የፍትሕ እና የፀጥታ አካላት ከሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ጋር በተተያያዘ ሰፊ ሥልጣን እና ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ፤ በግጭት ወቅት ተሳትፎ ሲኖራቸው ስራዎቻቸውን ከአለማቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ገዢ መርሆች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዴት መሥራት ይኖርባቸዋል? እነዚህን መርሆች ወደ የተቋማቱ ኦፕሬሽን ማንዋሎች እና የአሠራር ስርአቶች እንዴት ማካተት ይቻላል? በሚሉት ነጥቦች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ እና ቀጣይ ስትራቴጂ ለማመላከት መሆኑን ገልፀዋል። ይህ አካሄድ የአሰራሮቻችንን ቅቡልነት፡ ህጋዊነት እና የተቋማትን ተጠያቂነት ከማረጋገጥ አንጻር ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም አመልክተዋል።በተመሳሳይ የሚኒስትሮች ግብረኃይል ሰክሬታሪያት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ካሳ የመድረኩን ዓላማ በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን፤ ዎርክሾፑ ስኬታማ እንዲሆን የቴክኒክ፡ የፋይናንስ እና የማስተባበር ስራዎችን ለሰራው የዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በራሳቸውና በጽ/ቤታቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

Tagged Under: Conflict Resolution • International Humanitarian Law • Northern Ethiopia Conflict
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች