በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተፈጠረው ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎችን በተመለከተ የተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ስራዎች ላይ መግለጫ ተሰጠ
በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፣ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ ካሳ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ በአገሩቱ ሰሜናዊ ክፍል በተፈጠረው ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎችን በተመለከተ የተከናወኑ የወንጀል ምርመራ ስራዎች ላይ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ግብረ-ኃይሉ በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል በተፈጠረው ግጭት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎችን በተመለከተ የተገኙ ግኝቶችን እንዳብራሩት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የምርመራና ክስ ንዑስ ኮሚቴው በምርመራ ባገኘው መሠረት በንጹሀን ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ከባህልና ማኅበራዊ ሁኔታ ያፈነገጡ ጾታን መሠረት ያደረጉ ድርጊቶች፣ በቢሊየን የሚገመቱ የመንግሥትና የግለሰብ ንብረት ዘረፋዎች እና ሌሎች ወንጀሎችም በስፋት እና በተደራጀ ሁኔታ መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህ የምርመራ ሂደት 11 የምርመራ ቡድንንና 158 ባለሙያዎች ሙያዊ ሥልጠና ወስደው ምርመራውን ማከናወናቸው የተጠቆመ ሲሆን በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ክልሉ በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር በመሆኑ ለመመርመር አለመቻሉን ጠቁመው ግብረ-ሃይሉ አብዛኛውን ምርመራ በአማራና አፋር ክልል፣ በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እና ሌሎች ግጭት በነበረባች ቦታዎች ላይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች ላይ ምርመራ ተደርጎ የተገኘ ግኝት የመጀመሪያ ሪፖርት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመሆኑም በምርመራ ሂደቱ በተገኘው ግኝት መሠረት በአማራና አፋር ክልሎች በተከናወነው ምርመራዎች 2831 ሰዎች መገለዳቸው እና 452 ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ የታወቀ ሲሆን 36 ሰዎች የደረሱበት ቦታ ሳይታወቅ ተሰውረዋል ተብሏል፡፡
26,334 ቤቶች ደግሞ መቃጠላቸው መታወቁን የምርመራ ቡድኑ ያረጋገጠ ሲሆን 865,627 ኩንታል እህል መውደሙ፣ 411,048 የቁም እንስሳት መገደላቸው እና ከ2500 በላይ የጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች መውደማቸውን በሪፖርቱ ግኝት ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በምርመራው 175 ወረዳዎችን ለማካለል ተሞክሮ በተሰራው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ስራ በአማራ ክልል 9 ሺህ 552 የምስክሮች ቃል በአፋር ክልል 517 የምስክሮች ቃል የተሰማ ሲሆን በሁለቱም ክልሎች 3,387 የሰነድ ማስረጃ 2,599 የፎቶና የተንቀሳቃሽ ምስል ሰነዶችም ቀርበው ምርመራ እንደተደረገባቸውም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከፍርድ ውጪ ግድያ ከተፈጸመባቸው 2 ሺህ 831 ንጹሃን ዜጎች አብዛኛዉ በሽብር ቡድኑ ህወሓት የተፈጸመ ሲሆን በሰሜን ሸዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ደግሞ የሽብር ቡድኑ ሸኔ ከህወዐት ጋር በቅንጅት ግድያውን መፈፀሙ እንደተረጋገጠ ተጠቅሷል፡፡
በመግለጫው በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት በተመለከተ የመነግስት አቋም ምን እንደሆነ በዝርዝር ቀርቧል፡፡