ሙሃመድ ክፍሌ የተባለው ተከሳሽ ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 ስዓት በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ካራ ጋቢሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ8 ዓመት ዕድሜ ያላትንና በራሱ ቁጥጥር ስር የሚያሳድጋትን የእንጀራ ልጁን ከትምህርት ቤት ስትመጣ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አፏን አፍኖ አስገድዶ ከደፈራት በኃላ እናቷ ከስራ መጥታ ውሃ ስጪኝ ስትላት መንቀሳቀስና ከመቀመጫዋ መነሳት ባለመቻሏ እናቷም ስትጠይቃት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ እንደሚደፍራት እና ቢላ ይዞ “ብትናገሪ እንችንም እናትሽንም እገላችኋለሁ“ እያለ ያስፈራራት የነበረ በመሆኑ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ ቁጥር 627/1/እና 627/4/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለአካለ መጠን ያልደረሰችን ልጅ በተለያዩ ቀናት እና ጊዜ በተደጋጋሚ አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍ/ቤት ቀርቧል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጠውም ተከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ክስና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ ፍ/ቤቱ በተከሰሰበት ወንጀል የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፎበታል፡፡
በመሆኑም የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ 7 ኛ ወንጀል ችሎት ተካሣሹን ያስተምራል ፣ያርማል ሌላውንም የማኅበረሰብ ክፍል ያስጠነቅቃል በማለት በ15 (አስራ አምስት) ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡