በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የባንክ ሥራ በመሥራት ሀገሪቷ ልታገኝ የነበረውን ከ4 ሚሊዮን 515 ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ባደረገው ሳሙኤል እጓላ ላይ ክስ መሰረተበት፡፡
ክሱ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው
ተከሳሽ ሳሙኤል እጓለ አለሙ በእስር ይገኛል
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሹ የባንክ ሥራን ለመሥራት ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖረው ካልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የአሜሪካ፣ አዉሮፓና አረብ ሀገራት የሚገኙ ግለሰቦች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ሲፈልጉ እዚያው ሀገር የሚገኙ ያልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ገንዘቡን በመሰብሰብ የሚላክላቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር፣ የባንክ ሂሳብ ቁጥር እና የገንዘቡን መጠን በሚያስተላልፉለት መረጃ መሠረት ገንዘቡን አትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ በርካታ ግለሰቦች በስሙ የከፈታቸዉን የተለያዩ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች በመጠቀም ከ 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት በአጠቃላይ ተከሳሹ 182 ሚሊዮን 993 ሺ 953 ብር ከ49 ሳንቲም ከውጭ ሀገራት ገንዘብ ለተላከላቸው ሰዎች በማስተላለፍ ገንዘቡ በሕጋዊ ገንዘብ አስተላላፊዎች አማካኝነት ወደ ሀገር ዉስጥ ገብቶ ቢሆን ኖሮ ሀገሪቷ ልታገኝ የነበረዉን 4 ሚሊዮን 515 ሺ 562 ከ47 ሳንቲም የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመዉ ያለ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የባንክ ሥራ መሥራት ወንጀል ተከሷል የሚል ነዉ፡፡
ተከሳሹ ክሱ በችሎት ደርሶት በንባብ የተሰማ ሲሆን የክሱ ማመልከቻ ላይ መቃወሚያ ካለው ለመቀበል ለታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ሲቀጠር፤ተከሳሽ ዋስትና እንዲፈቀድለት በጠበቆቹ አማካኝነት ያቀረበው ጥያቄ ላይ ዐቃቤ ሕግ ዋስትናውን በመቃወም ክርክር ያደረገ በመሆኑ ችሎቱም ተከሳሹ የዋስ መብቱ ተነፍጎ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡