በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ፍቃዱ ደርበው፣ 2ኛ አያልሰው አባይ፣ የተባሉ ሁለት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት አስበው ሀምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ባጃጅ በኃይል ለመስረቅ ተስማምተው እና ተዘጋጅተው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጉልት ከሚባለው ቦታ በመሄድ ሟች ፍቃዱ ተሾመ ይነዳት የነበረውን ንብረትነቱ የሌላ ግለሰብ የሆነ ባጃጅ ተኮናትረው ወደ ቆሬ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ሁለቱም ተከሳሾች ከሟች ኋላ በመቀመጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 02 ባቱ ኮንደሚኒየም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ 1ኛ ተከሳሽ በምልክት ውጋው በማለት ለ2ኛ ተከሳሽ ሲነግረው 2ኛ ተከሳሽም ሟችን በቢላዋ አንገቱ ላይ ሲወጋው 1ኛ ተከሳሽም ራሱን እንዳይከላከል በለበሰው ልብስ አንገቱ ላይ አንቆ ሲይዘው 2ኛ ተከሳሽ በድጋሜ ሟችን ትክሻው አካባቢ ሲወጋው ሟች ከባጃጁ ላይ ወርዶ አስፓልት ዳር ወድቆ ብዙ ደም ፈሶት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ ባጃጇን እየነዳ ወደ ወልዲያ ወስደው ለመሸጥ አስበው ሸዋሮቢት ላይ አንደኛውን የዐቃቤ ሕግ ምስክር ጠርተው 1ኛ ተከሳሽ በፔስታል ጠቅልሎ የባጃጁን ሰሌዳ አስቀምጥ ብሎ ሰጥቶት ምስክሩም ሰሌዳውን አስቀምጦላቸው አብረው ወደ ወልዲያ እየሄዱ እያለ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ ይዟቸው ፖሊስ ባጃጇን ሲፈትሽ ሟችን የወጉበት ቢለዋ የተገኘ በመሆኑ በፈፀሙት ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ክስ ቀርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷቸው ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን በዚህም ሁለቱም ተከሳሾች በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡