የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ታምራት ኃይሌ የተባለው ተከሳሽ በ2 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን፣ በ1ኛ ክሱ ላይ መስከረም 6 ቀን 2015 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ኦሮሚያ ኮንደሚኒየም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ በፍርድ ቤት መበርበሪያ ትእዛዝ በተደረገ ብርበራ እንደእውነተኛ አድርጎ ለማዘዋወር በማሰብ ህጋዊ መገበያያ የሆኑትን የኢትዮጵያ ባለ ሁለት መቶ ኖት መጠኑ 6 ሺ ብር የሆነ እና የአሜሪካን ዶላር የባለ አንድ መቶ ኖት ብዛቱ 600 የሆኑትን ለመስሪያነት የሚያገለግሉትን ኮምፒዩተር፣ ከለር ፕሪንተር እና የተለያዩ ቀለሞች በማዘጋጀት ስካን በማድረግና ከለር ፕሪንት በማድረግ ሀሰተኛ ገንዘቦችን የሰራ በመሆኑ ሀሰተኛ ገንዘብ መሥራት ወንጀል ተከሷል፡፡
በ2ኛ ክሱ ደግሞ ከላይ በ1ኛ ክሱ በተጠቀሰው ቀንና ቦታ በተደረገ ብርበራ ጥቅምን ወይም መሻሻልን ለማስገኘት በማሰብ ግላዊ ሁኔታን የሚገልጹ አራት የልደትና አንድ የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣ በአንድ ግለሰብ ስም የተዘጋጀ የንግድ ስራ ፈቃድ፣ የነዋይ ቻሌንጅ አካዳሚ የመሰናዶ ት/ት ቤት በሁለት ግለሰቦች ስም የተዘጋጀ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የት/ት ውጤት የያዘ ትራንስክሪፕት፣ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ዲግሪ በአንዲት ግለሰብ ስም የተዘጋጀ የተማሪ አጠቃላይ የውጤት ማስረጃ የሆኑትን፣ ለመስሪያነት የሚያገለግሉትን ኮምፒዩተር፣ ከለር ፕሪንተር እና የተለያዩ ቀለሞች በማዘጋጀት ስካን በማድረግና በከለር ፕሪንት በማድረግ ሀሰተኛ የምስክር ወረቀቶችን የሰራ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦበት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በሁለቱ ክሶቹ ላይ በ7 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡