በቅርቡ የፀደቀው ሀገር አቀፍ የነጻ የህግ ድጋፍ ስትራቴጂ የስራ ምረቃ መርሃ ግብር ተካሄደ

Inaugural Program of the Recently Approved National Free Legal Aid Strategy Was Held

ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ፍትሕ የማግኘት መብትንና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሕን ብሎም ሌሎች መሠረታዊ መብቶችንናነጻነቶችን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በዚህ መነሻነት አገልግሎቱን ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ነገር ግን አገልግሎቱን ተደራሽ፣ ወጥነት፣ቀጣይነት እና ጥራት ባለው መልኩ ከመስጠት እና በአገልግሎቱ ሰጪ እና ባለድርሻ አካላት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር ከመዘርጋት አንፃር ክፍተቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ መቀረጽ እንዳለበት ተወስኖ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ስትራቴጂውን የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ ቆይቶ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

የስትራቴጂውን መፅደቅ ተከትሎ ወደትግበራ ለማስገባት የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የማብሰሪያ መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው የመድረኩ ዓላማ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂን ወደስራ ለማስገባት መፅደቁን ማስተዋወቅ እና በቀጣይ የጋራ የስራ አቅጣጫ ለመያዝ መሆኑን ገልፀው ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸዉ በህገ መንግስቱ የተደነገገ ቢሆንም ጠበቃ አቁሞ ለመከራከር የገንዘብ አቅም የሌላቸው በመሆኑ እና በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አክለውም ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች እና በሀገራችን ህገ መንግሥት የተካተተ መብት መሆኑን፣ መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ አካላት ሲሰራ መቆየቱን፣ የሚሰጠው አግልግሎት የተቀናጀ አለመሆኑን፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ ስትራቴጂው እንዲዘጋጅ መደረጉን እና በቀጣይ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና አሰራሮች እንደሚዘጋጁ አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን በመወከል በመድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የረጅም ዘመን ዳኝነት አገልግሎት ያላቸው እና አሁንም በማገልገል ላይ የሚገኙት የተከበሩ አቶ ብርሃኑ አመኑ ሀገራችን ባፀደቀቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ትኩረት ከተሰጣቸው መብቶች መካከል ፍትሕ የማግኘት መብት አንዱ መሆኑን፣ የተከሰሱ ሰዎች ጠበቃ ማቆም ባለመቻላቸው ፍትሕ የሚጓደል ከሆነ በመንግሥት በነጻ ጠበቃ ሊመደብላቸው እንደሚገባ በሕግ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች ስር የተደራጀው የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት በከባድ ጉዳዮች ላይ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ እና ሕፃናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ለህጻናት አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱን ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያለ ቢሆንም የተደራሽነት ችግር ያለ መሆኑን፣ ያለውን የአቅም ውስንነት፣ የተደራሽነት፣ እና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እልባት ለመስጠት ስትራቴጂው መፍትሔ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠል የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኦሞድ ሰዎች በተፈጥሮ የሚያገኟቸውን መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች (ህጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች) ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻ ከፍተኛ አስተዋዕፆ አለው ብለዋል፡፡ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉደዮች ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ልዩ ድጋፍ በሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይተዋል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ቢሰሩም አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ ጥራት ያለው እና ተደራሽ ነው ለማለት አይቻልም ብለዋል፡፡

አክለውም አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሸ ለማድረግ እና ጥራቱን ለማሻሻል ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው እና ስትራቴጂው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ከመለየት እና የቅንጅታዊ አሠራር ስርዓት ለመዘርጋት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ለሴቶች፣ ህጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ያለው ትርጉም ትልቅ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በመጨረሻም ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱንነ በተሻለ ሁኔታ ለመስጠት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመቀጠል በስትራቴጂው ይዘት ዙሪያ ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ገለፃውን ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አዲስ ጌትነት ሲሆኑ በገለፃቸው እስካሁን ሲሰጥ የነበረው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ምን እንደሚመስልና የሚስተዋሉትን ችግሮች፣ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ዓላማ፣ የያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እና ማስፈፀሚያ ስልቶችን አብራርተዋል፤ የመድረኩ ተሳታፊዎችም የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አንስተው ውይይት የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎች በዋናነት ስትራቴጂው መፀደቁ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው እና ለመተግበርም ቁርጠኛ መሆናቸውን በተለያየ መንገድ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው እና ክብርት ወ/ሮ አለሚቱ ኦሞድ መድረኩን እየመሩት በቀረበው ገለፃ ላይ በተሳታፊዎች ውይይት የተደረገ ሲሆን ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቱ መፅደቁ በተለይ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅትና በትብብር እንዲሰሩ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻ መድረኩን የዘጉት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በማጠቃለያቸው ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂውን ለመተግበር በቀጣይ የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት እና የአሠራር ሥርዓቶችን የመዘርጋት ስራ እንደሚሰራ፣ ስትራቴጂውም ታትሞ በቅርብ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚሰራጭ፣ ህብረተሰቡ ስለነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና ህጎች ግንዛቤ እንዲኖረው የንቃተ ሕግ ትምህርት የመስጠት ስራ በሰፊው እንደሚሰራ ገልጸው የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እንዲሰሩ እና ለስትራቴጂው ትገበራ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈው መድረኩ ተጠናቋል።

Tagged Under: act • african charter on the rights and welfare of the child • aid • Convention on the Rights of the Child • convention on the rights of the child (crc) • court • decree • free • Free Legal Aid • judge • judicial • judiciary • law • legal • Legal Aid • legal aid services • legal aid strategy • legislation • National • national free legal aid strategy • national legal aid strategy • Policy • pro • proclamation • program • rate • Regulation • statute • Strategy • tribunal
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች