በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የኢ.ፌ.ዴ. ሪ. የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ለመደንገግ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት የተሰጡትን አስተያየቶች በግብዓትነት መውሰዱን ገለጸ።
ሰሞኑን በተካሄደው በአስረጂ እና ባለድርሻ አካላት መድረክ፤ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ኢሳ ቦሩ፣ ረቂቅ አዋጁ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት ባለድርሻ አካላት በአካል ተገኝተው የሰጡት ሐሳብ እና አስተያየት ሁሉ ዋጋ እንዳለው አስረድተዋል።
በረቂቅ አዋጁ የተመላከቱት ዝርዝር የሕግ ድንጋጌዎች ዝርዝር አፈጻጸሞች እንደሚያሻቸው በተጠቆመበት በዚህ ይፋዊ የሕዝብ የውይይት መድረክ፤ ሌሎችም ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነባቸው አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። እናም፤ ቋሚ ኮሚቴው እንደየተገቢነታቸው እንደሚጠቀማቸው ከመድረኩ መሪዎች ተመላክቷል።
በመድረኩ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው በኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረው የወንጀል ሕግ አሁን ካለው ሕገ-መንግሥት ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፤ የተዘጋጀውም ረቂቅ ሕግ ለሚፈጸሙ ውስብስብ ወንጀሎች እልባት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በረቂቁ ላይ ከ10 ዓመት በላይ በየደረጃው የፍትሕ አካላት ሲወያዩበትና ለማሻሻል ሲሰሩበት የቆየ እና ሰፊ ግብዓት የተሰባሰበበት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በ1949 ዓ.ም ህጉ ሲወጣ ይፈጸም የነበረው ወንጀል የተለየ እና አሁን የሚፈጸመው ወንጀል እየተወሳሰበ መምጣን ጠቅሰው፤ አዲሱ ረቂቅ ሕግ ሚዛን የጠበቀና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
በወንጀል ፍትሕ ስርዓት የማኅበረሰብን ተሳትፎ የሚያጠናክር፣ የወንጀል ጉዳዮችን ሰላማዊ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ እንዲሁም ለወንጀል ጉዳዮች ዘለቄታዊ ዕልባት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በረቂቁ የዕርቅና የጥፋተኝነት ድርድር የተካተተበት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።
በመድረኩ በተጨማሪ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የሕግ ክፍል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በውይይቱ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ መዋላቸውን መረዳት ተችሏል።
ምንጭ፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት