በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ 384 ኩንታል ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ቡና በሁለት ተሽከርካሪዎች በመጫን በወሰዱ 4 ተከሳሾች ላይ ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ መሰረተባቸው፡፡
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች 1ኛ ተስፋ አየለ፣ 2ኛ ፍሪሳ ሞሲሳ፣ 3ኛ ጌታቸው ፈቃዱ፣ 4ኛ ሹሜ ዘውዴ የተባሉ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/1/ለ/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በክሱ መሠረት ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው ቀርሳ ኢንዱስትሪ መንደር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ካልተያዙ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በአንድ የጥበቃና የሰው ኃይል አገልግሎት ኃ/የተ/የግል ማህበር በኩል የግል ተበዳይ ድርጅት የሆነውን የዋልያ ብረታ ብረት ኃ/የተ/የግል ማህበርን ለመጠበቅ ተቀጥረውና በእለቱም ተረኛ የጥበቃ ሠራተኛ ሆነው ተመድበው 4ኛ ተከሳሽ በግል ተበዳይ ድርጅት ውስጥ የኮንትራት ጫኝና አውራጅ ሠራተኛ ሆኖ ተቀጥሮ ሲሰራ መስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7፡00 ሲሆን ያልተያዘው አንድ የድርጅቱ ጥበቃ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የዋልያ ብረታ ብረት ኃ/የተ/የግል ማህበር ግቢን የእለት እንቅስቃሴ ለመቃኘት የተገጠመውን የተንቀሳቃሽ ምስል መቅረጫ የደኅንነት ካሜራ እንዳይቀርጽ በማቋረጥ እንዳያገለግል ካደረገ በኋላ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸዉ በቀጣዩ የወንጀል ዝርዝር ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በዚሁ መሠረት 1ኛ ተከሳሽ የድርጅቱ ቀሪ ጥበቆች ወደ ወንጀሉ ስፍራ እንዳይቀርቡና እንዳይመለከቱ በመጠበቅና ካልተያዘው የድርጅቱ ጥበቃ ጋር ወንጀሉ ተፈፅሞ ሲጠናቀቅ 200 ሺ ብር እንደሚከፈለው በመስማማት ተሳትፎ ማድረጉ በክሱ ተገልጧል፡፡
2ኛ ተከሳሽ ካልተያዘው የድርጅቱ ጥበቃ ጋር በመመሳጠር የግል ተበዳይ ድርጅት ዋና በርንና የመጋዘኑን በር አብሮ ሰብሮ በመክፈት፣ ሌሎች ግለሰቦችና የድርጅቱ ሌሎች ጥበቃዎች የወንጀል ድርጊቱን እንዳያዩ በመጠበቅ ተሳትፎ በማድረግ የግል ተበዳይ ድርጅት ንብረት የሆነው ቡና የሚወሰድበትን ጊዜ በማቀድ መሳተፉን የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል፡፡
3ኛ ተከሳሽ በበኩሉ በተመሳሳይ ካልተያዘው የድርጅቱ ጥበቃ ጋር ከወንጀሉ መፈጸም በፊት በመገናኘት የወንጀሉን አፈፃፀም በጋራ በማቀድ፣ ቡናው የሚጫንበትን መኪና በማቅረብ፣ የሚጭኑ መኪኖችንና ግለሰቦችን ወደ ግል ተበዳይ ድርጅት በመውሰድ እንዲገቡ ሲያደርግ ካልተያዙ አምስት ግብረ-አበሮቻቸው ውስጥ ሶስቱ ክላሽንኮፍ የጦር መሳሪያ ይዘው ወደ ግል ተበዳይ ድርጅት ከገቡ በኋላ ድርጅቱን በመጠበቅ ላይ ተሰማርቶ ይገኝ የነበረውን ጥበቃ አንገቱን አንቀው በመያዝና በክላሽንኮፍ መሳሪያ ሰደፍና አፈሙዝ ጭንቅላቱንና የተለያየ የሰውነት ክፍሉን በመምታት ጉዳት እንዲደርስበት ካደረጉ በኋላ ለብሶት በነበረው ጨርቅ እጅና እግሩን በማሰር እንዲሁም ድምጽ እንዳያሰማ አፉን በፕላስተር በማፈን በድርጅቱ ግቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ በማስገባት ካልተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል አንድ ግለሰብ እንዲጠብቀው ማድረጉ በክሱ ተገልጧል፡፡
4ኛ ተከሳሽ ካልተያዘው የድርጅቱ ጥበቃ ከሆነው ግብረ አበሩ ጋር በመመሳጠርና በድርጅቱ ውስጥ በኮንትራት ጫኝና አውራጅ ሠራተኛ መሆኑን በመጠቀም የድርጅቱ ንብረት የሆነውን ቡና 3ኛ ተከሳሽ ባቀረባቸው መኪኖች ላይ በመጫንና በመደርደር ተሳትፎ የዋጋ ግምቱ 14 ሚሊዮን 562 ሺ 432 ብር የሚያወጣ 384 ኩንታል የታጠበ ለውጭ ገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ቡና በሁለት ተሽከርካሪዎች በመጫን የወሰዱ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ በዐቃቤ ሕግ ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾች በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ ደርሷቸው በችሎት የተነበበላቸዉ ሲሆን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ የለንም ያሉ ሲሆን፣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በበኩላቸዉ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፤ ፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡