በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ሕግ ከ713 ሺ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸውን 20 ኮምፒዩተሮች እና 2 ፕሪንተሮች ለጥገና ወደ ድርጅቶች ገብተው ጥገናቸው ሲጠናቀቅ ወደ ባንኩ ገቢ ማድረግ ሲገባቸው ወስደው ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ ተከሳሾች ላይ ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ክስ መሰረተባቸው፡፡
በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ዳዊት ጫልቺሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛጉዌ ህንፃ በንብረት ክፍል የጉልበት ሠራተኛ የነበረ፣ 2ኛ ተከሳሽ አብርሃም በላይነህ በግል የሚሰራ ሲሆን፣ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁ.881/2007 አንቀጽ 31(1)፤ (2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
በክሱ ዝርዝር ላይ 1ኛ ተከሳሽ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በኮሜርሻል ኖሚኒስ በጉልበት ሠራተኛነት ተቀጥሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛጉዌ ህንፃ ኔትወርክ ሳፖርት እና ሮል አውት ክፍል በሚያገለግልበት ወቅት በግል ስራ ከሚተዳደረው 2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ 1ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የባንኩ ንብረት ክፍል ሠራተኛ ባጋጠማት ህመም ምክንያት ስራውን በእምነት ተረክቦ በሚሰራበት ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኔትወርክ ሳፖርት እና ሮል አውት ክፍል ውስጥ ለጥገና ገቢ ከሆኑ እና የዋጋ ግምታቸው 713 ሺ 782 ብር ከ63 ሳንቲም የሆኑትን 20 ኮምፒዩተሮች እና 2 ፕሪንተሮች፤ 1ኛ ተከሳሽ 14 ኮምፒዩተሮችን በራሱና ሌላ 1 ኮምፒዩተር ደግሞ በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ጥገና ወደ ሚደረግበት ድርጅት ገቢ ከሆኑና ጥገናቸው የተጠናቀቁ ኮምፒዩተሮችን ከድርጅቱ ከተረከበ በኋላ ወደ ባንኩ ገቢ ማድረግ ሲገባው ለራሱ የወሰደ በመሆኑ፤ በተመሳሳይ 2 ፕሪንተሮች ለጥገና ወደ ሌላ ድርጅት ገብተው ጥገናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ተረክቦ ወደ ባንኩ ገቢ ማድረግ ሲገባው የወሰደ በመሆኑ፤ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ በባንኩ የተለያዩ ክፍሎች ለጥገና ወደ ንብረት ማከማቻ ክፍል ከገቡት እቃዎች ውስጥ አምስት ኮምፒዩተሮችን የክፍሉ እውቅና በሌለው እና በተጭበረበረ የበር የዕቃ ማውጫ ፍቃድ እንዲወጣ በማድረግ የወሰደ በመሆኑ፤
2ኛ ተከሳሽ ደግሞ የተቋሙ ሠራተኛ ሳይሆን ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የባንኩ ንብረት የሆነውን ኮምፒዩተር ለጥገና ወደ ድርጅቱ ገቢ በማድረግ 1ኛ ተከሳሽ እንዲረከብ ትእዛዝ በመስጠት 2ኛ ተከሳሽ ጥገናቸው የተጠናቀቁ 7 ኮምፒዩተሮችን ተረክቦ ወደ ባንኩ ገቢ ማድረግ ሲገባው ለራሱ የወሰደ በመሆኑ፤
በአጠቃላይ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በእምነት ተረክቦ በሚሰራበት ወቅት የዋጋ ግምታቸው 713 ሺ 782 ብር ከ63 ሳንቲም የሆኑትን 20 ኮምፒዩተሮች እና 2 ፕሪንተሮች መካከል 15 ኮምፒዩተሮች እና 2 ፕሪንተሮችን ጥገናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ከሁለት ድርጅቶች ወስደው ወደ ባንኩ ገቢ ማድረግ ሲገባቸው ለራሳቸው ጥቅም ያዋሉ በመሆኑ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ በባንኩ የተለያዩ ክፍሎች ለጥገና ወደ ንብረት ማከማቻ ክፍል ከገቡት እቃዎች መካከል 5 ኮምፒዩተሮችን ወስዶ ለግል ጥቅሙ ያዋለ በመሆኑ ተከሳሾች ለራሳቸው ከፍተኛ ጥቅም ያገኙ እና በባንኩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ በፈጸሙት ከባድ የእምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶት ከጠበቃ ጋር ተማክሮ ሲቀርብ ክስ ለመስማት እና 2ኛ ተከሳሽን ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡