የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ሲሳይ በርሄ፣ 2ኛ ክብረወሰን ዋለልኝ፣ 3ኛ መሀመድ አምዲሶ፣ 4ኛ ይዘዝ አማረ፣ 5ኛ ፊልሞን አብይ፣ የተባሉ አምስት ተከሳሾች በፈፀሙት የውንብድና ወንጀል ጽኑ እስራት ተፈረዶባቸዋል፡፡
ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ነሀሴ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ጤና ጣቢያ አካባቢ ተከሳሾች ወንጀል ለመሥራት አቅደውና ተስማምተው ለዚሁ ወንጀል ድርጊት መፈጸሚያ የሚሆን ሁለት ቪትስ መኪናና ሽጉጥ በመያዝ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ በኃላፊነት የሚመሩት የበሉና ኤክስፖርት ቄራ ኃ/የተ/የግል ማህበርን ተከሳሾች የያዙትን መኪና ድርጅቱ ፊት ለፊት አቁመው የድርጅቱ ጥበቃ የሆነውን 1ኛ ተከሳሽ መኪናችን ተበላሽቶ ነው ውሃ አለ ወይ ብሎ በማዘናጋት ከኋላው ስልክ እያወራ በመጠጋት አንገቱን ሲያንቀው፣ 2ኛ ተከሳሽ በቦክስ ደጋግሞ እየመታው መሬት ላይ ጥለውት እራሱን መከላከል በማይችልበት ደረጃ ላይ እያለ በድርጅቱ የሚገኙ 1ኛ 5 የስጋ መፍጫና መቁረጫ ማሽኖች፣ 2ኛ 3 ሚዛን፣ 3ኛ 1 ቴሌቪዥን፣ 4ኛ 6 ኮምፒየተሮች፣ 5ኛ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 643 ሺ 414 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን ሊወስዱ ሲሉ ሌላው የጥበቃው ባልደረባ ድምጽ ሰምቶ ሲወጣ 1ኛ ተከሳሽ በያዘው ሽጉጥ ወደ ጥበቃው ተኩሶበት የሱፐር ማርኬቱን መስታወት በጥይት በመስበር ሌሎች 3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ከመኪናው ወርደው ሰውን ሲጠባበቁ የነበሩትን መኪናውን አዘጋጅተውት በማንቀሳቀስና ሰሌዳቸውን ፈተው በፍጥነት ያመለጡ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/፣ 27/1/ እና 670 መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት የውንብድና ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ 2ኛ፣ 4ኛና 5ኛ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው፣ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ማቅረብ ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ ያሳረፈ ሲሆን በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በ13 ዓመት፣ 2ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ላይ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ ላይ ደግሞ በሌለበት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡