ተቋሙ በሀገር ሰላም እና በሕዝብ ጥቅም ላይ ከባድ ጉዳት በሚያደርሱ ትላልቅ ወንጀሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ እና የህጎች ተፈጻሚነትን ከመከታል አንጻር ባለፉት 4 ዓመታት የለውጥ ሂደት ውስጥ የወጡ ህጎችን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ተገቢው ጥረት እንደሚደረግም ተናግሯል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት በተካሄደ የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በተካሄደ ውይይት ላይ ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት የያዘ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በዚህ የዕቀድ እና በጀት ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ደሳለኝ መንግስቴ በቀረበው ሪፖርት የወንጀል ሕጉን ከማስከበር አንጻር በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ፣ በኢኮኖሚ እና በሙስና የወንጀሎች ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ምርመራቸው ተጠናቆ ከቀረቡለት 4,582 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 4,242 የምርመራ መዝገቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች የተሰጡባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ 340 መዝገቦች በዐቃቤ ሕግ እጅ የሚገኙ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔ አፈፃፀምን በተመለከተም በሦስቱ የወንጀል ጉዳዮች የቀጥታ ክስ የክርክር መዛግብት በ3,259 መዛግብት ላይ ክርክር የተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በድምሩ 1076 መዛግብት ላይ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ውሳኔ ከተሰጠባቸዉ ዉስጥ ዐቃቤ ሕግ በ1013 መዛግብት ላይ ተከሳሾች የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ እንዲተላፍባቸው ያስደረገ ሲሆን በ63 መዛግብት ላይ ደግሞ ተከሳሾች በነጻ ተሰናብተዋል፡፡ በዚህም መሠረት የዓቃቤ ሕግ የመርታት ምጣኔን ከመዛግብት አንጻር ስንመለከተው አማካይ ውጤቱ 94% ነው፡፡ ፍርድ ቤት ቅጣት በጣለባቸው መዛግብት ላይ በድምሩ 2,615 ተከሳሾች የተለያዩ ቅቶች እንዲጣልባቸው ማድረግ ተችሏል፡፡
በልዩ ልዩ ወንጀሎች የወንጀል የምርመራ መዛግብት ውሳኔ የመስጠት አፈጻጸምን በተመለከተ ምርመራቸው ተጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ ከደረሱት 42,565 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ በድምሩ 34,387 (99.8%) መዝገቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች በዐቃብያነ ሕግ ዉሳኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ እንዲሁም ክርክር ከተደረገባቸው 37,426 መዛግብት ውስጥ 16,232 መዛግብት ላይ ፍርድ ቤት ዉሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ፍርድ ከተሰጠባቸው መዛግብት መካከል ደግሞ 15,646 መዛግብት ተከሳሾች ጥፋተኛ እንዲባሉ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህም የዐቃቤ ሕግ የመርታት ምጣኔን ከመዛግብት አንጻር ስንመለከተው 96.4% መድረስ ችሏል፡፡ በተከሳሾች ብዛት አንጻር ፍርድ ቤቶች በ22,217 ተከሳሾች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች የተሰጡ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ 21,471 በሚሆኑት ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ ያሸነፈ በመሆኑ የተለያዩ ቅጣቶች ሊጣልባው ችሏል፡፡ በአጠቃላይ ከእስራት ቅጣቶች በተጨማሪ በጥፋተኞች ላይ የተጣለን የገንዘብ መቀጮ ተከታሎ ገቢ እንዲሆን በማድረግ ወደ 7 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የመንግሥትና የሕዝብ ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በተመለከተ 2,418 የምክር አገልግሎት ጥያቄዎች ቀርበው በሁሉም ላይ ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን የውልና ሌሎች ረቂቅ ሰነዶችን ከመመርመር አንጻር ለቀረቡ 51 ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በተያያዘም ከድርድር አፈጻጸም አንጻር በተከናወነ ስራ የመንግሥት ተቋም ተጠይቆ የነበረ 7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ካሳ ጥያቄ እንዲቀር የተደረገ ሲሆን 87,477.50 USD ዋጋ የሚያወጡ መድኃኒቶችን የማስመለስ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከግልግል ዳኝነት አፈጻጸም እና የፍትሐብሄር ክርክር ተቋሙ ያከናወናቸው ተግባትም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
ከሕግ ምክር እና ማርቀቅ ስራ ጋር በተያያዘም ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 12 ሕችን አርቅቋል፤በ94 ጉዳዮች ላይ የሕግ ምክር የሰጠ ሲሆን እንዲሁም በ184 ጉዳዮች ላይ የሕግ እርማት መሰጠት ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል 997 መመሪያዎችን ከተቋማት ተቀብሎ የመዘገበ እና በተቋሙ ድረ ገጽ እንዲጋራ ያደረገ ሲሆን የተጠቃለሉ ሕጎችን አሳትሞ ለተገልጋዮች ማሰራጨት መቻሉን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በገለጻው ከህጎች ተፈጻሚነት መከታተል፣ በሰዎች የመነገድ እና ድንበርን የማሻገር ወንጀልን ከመከላከል፣ ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ ከጠበቆች አገልግሎት እና ነጻ የሕግ ድጋፍ፣ ከዐለም ዐቀፍ የሕግ ትብብር፣ ከንቃተ ሕግ ትምህርት ስርጭት እና አቅም ግንባታ፣ ከይቅርታ አሰጣጥ፣ በወንጀል የተገኘ ሀብትን ከማስመለስ፣ ምስክሮችን ከመጠበቅ እና መሰል ጉዳዮች አንጻር በተቋሙ የተከናወኑ ተግባራትን የሚመለከቱ ነጥቦች በዝርዝር ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡
ቀጥሎም የተቋሙ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
ውይይቱን የመሩት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታዎች አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና አቶ አለምአንተ አግደው የውይይት መድረኩን ሲያጠቃልሉ ዕቅዱ አዲስ ጅማሮን እና ምልከታን በውስጡ ያቀፈ ሲሆን የባለሙያዎችን ሥነ ምግባር እና ሙያዊ ብቃት በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ በማድረግ ሀገራዊ በሆኑ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ገጥመዋት በነበሩት ግጭቶች ምክንያት በግለሰቦች እና ሀገር ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት ከግምት በማስገባት ወንጀል ከመከላከል ጀምሮ አጥፊን በሕግ የማስጠየቅ ስራው በተሻለ እንዲመራ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡
ህጎች ለወጡለት ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ እንዲቻልም በቅርብ ጊዜያት የሕዝብን መብት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚል የወጡ ህጎችን ተፈጻሚነት ከሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተገቢው የመከታተል እና ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ስራ እንደሚሰራም በዕቅዱ ተመላክቷል ተብሏል፡፡ የህጎቹን ተፈጻሚነት ሀገር አቀፋዊ ለማድረግም በ2014 በጀት የተጀመሩት የፌዴራል እና የክልል ፍትሕ ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ተጠናቅሮ እንዲቀጥል ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡
አሠራርን ከማዘመንም አንጻር ስራዎች ቀልጣፋ እና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ ሲሆን ይህም የተቋሙን እና አጠቃላይ የፍትሕ ስርዓቱን መረጃ አያያዝ በበለጠ ለማሻሻል እንደሚያግዝ ታምኖበት ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡