የንግድ ህጉን አዋጅ አፈጻጸም ለማጥናት የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚቴ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡
የነጋዴዎቸን፣ የባለሀብቶችን እና በሕጉ ጥቅማቸው በቀጥታ የሚነካ ባለድርሻ አካላት መብቶችን በሚዛናዊ ሁኔታ ለማስተናገድ፤ የኢትዮጵያን ዓለም-አቀፍ ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት ብሎም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ ሲባል የተሻሻለው የንግድ ህጉ ሚያዚያ/2013 ዓ.ም ጸድቆ ወደስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ አፈጻጸሙን ለማጥናት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋቋመው እንዲሁም በመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ የሚመራው የባለሙያዎች ኮሚቴ፤ አፈጻጸሙን አስመልክቶ እያካሄደ ላለው ጥናት ግብዓት ለማሰባሰብ ያግዘው ዘንድ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ንግግር ያደረጉት የሕግ አማካሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁም የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር ታደሰ ሌንጮ እንደተናገሩት፤ የንግድ ህጉ ዋና ፖሊሲ አስቻይ መሆን ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም 825 አንቀጾች ያሉት የንግድ ህጉ እነዚህን መሠረት በማድረግ ሊተገበር ይገባል ብለዋል፡፡
አክለውም የንግድ ህጉ ቴክኖሎጅን የሚከተል ከጊዜው ጋር የሚራመድና ቢቻል የወደፊቱን የሚተነብይ መሆን አለበት ሲሉ ተናግረው፤ አሁን የተሻሻለው ሕግም የ1952ቱ ዕጣ እንዲገጥመው አንፈልግም ህጉ ከወጣ መተግበር መቻል አለበት ሲሉ በአጽዕኖት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዶክተር ታደሰ ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላም የአፈጻጸም ጥናቱ ያለበትን ደረጃ ለመድረኩ የቀረበ ሲሆን፤ በጥናት ሰነዱ በአዲሱ የንግድ ሕግ የተደረጉ ማሻሻያዎች፣ በአተገባበሩ ላይ የታዩ ክፍተቶች፣ የትግበራ ምክረ-ኃሳቦች፣ ምክረ-ኃሳቦቹን ለማስፈጸም የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በተለይም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴ ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ያላቸውን ድርሻ በስፋት በሰነዱ ላይ ተመላክቶ በመድረኩ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡
በመጨረሻም ከመድረኩ የተለያዩ ኃሳቦች ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ለግብዓትነት የሚውሉት ነጥቦች ተወስደው የዕለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡