የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 58ኛ የከፍተኛ ደረጃ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልፀዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና በመመረጧ ምክር ቤቱን አመስግነው፣ ሀገራቸው ዓለም ዓቀፍ ትብብርን ለማጎልበት እና እየተስተዋሉ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተግዳሮቶችን ከሌሎች የምክር ቤቱ አባል ሀገራት ጋር በመሆን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በማፅደቅ፣ ዓለም ዓቀፍ ትብብርን በማሳደግ እና ቁልፍ የሕግ፣ የፖሊሲ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን በመተግበር በUDHR 75 ስር የገባችውን ቃል በመፈፀም ረገድ ተጨባጭ እርምጃ መውሰዷን እና በውጤቱም አጠቃላይ የሕግ ማሻሻያ ውጥኖቹ ተራማጅ ህጎች አንዲወጡ እና ተቋማትን ለማጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ወቅታዊ ግምገማ (UPR) ሂደት ውስጥ በንቃት ስታደርገው የነበረው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያወሱት ክብርት ወ/ሮ ሐና ሀገሪቱ በነሀሴ ወር 2024 የ4ተኛውን ዙር ሀገራዊ ሪፖርት አቅርባ 316 ምክረ-ሃሳቦችን ተቀብላለች ካሉ በኋላ በቀጣይም ሀገራቸው ተቀባይነት ያገኙ ምክረ-ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ ያለፉትን ኢ-ፍትሃዊነቶች ለማረም እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የወንጀል ተጠያቂነትን በማስፈን፣ እውነትን በማውጣት እና ብሔራዊ እርቅን እውን በማድረግ ላይ የተመሰረተ የተሟላ የሽግግር የፍትሕ ፖሊሲን በማውጣት ለውጤታማ ተግባራዊነቱ በንቃት እየሰራች ትገኛለች ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ሂደቱን አሳታፊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተአማኒነት ያለው ለማድረግ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ከሽግግር ፍትሕ በተጨማሪ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ህዝባዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኗንም አውስተዋል። ከነዚህ ሀገራዊ ጥረቶች ጎን ለጎን የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ለአህጉራዊ እና አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዘዴዎች ኢትዮጵያ የምታደርገው አስተዋፅኦ ሀገሪቱ ለሰላምና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት ሚኒስትሯ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በተሳካ ሁኔታ መተግበሩ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለው ይህ ስኬት መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ እና ከዚያም በላይ ያሉትን ተግዳሮቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
ወደፊትም ኢትዮጵያ በብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዘዴዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በትኩረት ትሰራለች፤ የሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት የሁሉንም መብቶች መከበር እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው ሀገራት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን እና ሌሎች የተጋላጭ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለችም ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ በንግግራቸው ማጠቃለያ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ላደረገው ትብብርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።