በወንጀል ፍትሕ ስርዓት ውስጥ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ማስረጃ ነው፡፡ ከማስረጃ አይነቶች ዝርዝር ውስጥ ደግሞ በቀደምትነት የሚጠቀሰው የሰው ምስክርነት /witness Testimony/ ነው፡፡ ሰዎች በስሜት ህዋሶቻቸው ያስተዋሉትን ጉዳይ ለፍትሕ ተቋማት በመጠቆማቸው ወይም ምስክር በመሆናቸው ምክንያት ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ይህንንም በመፍራት ሰዎች የወንጀል ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያዩ እንዳላዩ ሆነው ሲያልፉ መመልከት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም እንዲህ አይነት ችግር በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ የሚያስከትለውን በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት በ2003 ዓ.ም የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 699/2003ን አውጥቶ በስራ ላይ አዋለ፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ውበት ጋሻው እንደሚሉት የዚህ በስራ ላይ ያለው አዋጅ ዓላማ ሀገሪቱ ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ያለምንም ስጋት እና ፍራቻ የሚያውቁትን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በመግለጽ ወንጀልን በመከላከል ሂደት ውስጥ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ እና የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንዲችሉ የሚያስችል የተሟላ ጥበቃ ለማድረግ የሚረዳ የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖራት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ በዋናናትም በትልልቅ እና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የጥቅም ጉዳት በሚያስከትሉ ወንጀሎች ላይ ጥቆማ የሚሰጡም ሆኑ ምስክር ሆነው በችሎት ቀርበው የሚመሰክሩ ሰዎች በዚሁ የተወደደ ተግባራቸው ምክንያት ከሚደረስባቸው ማንኛውም ጥቃት መጠበቅ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዳይሬክተሯ አክለው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የሰው ምስክርነት ማስረጃ ወሳኝ በመሆኑ በእንክብካቤ ሊያዝ፤ በትኩረት ሊሰራበትም ይገባል ብለዋል፡፡
አዋጅ ቁጥር 699/2003 በዋናነት ስለ ምስክርነት እና ጠቋሚነት ምንነት ትርጉም የሰጠ እና ለእነኚሁ ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ከግምት የሚገቡ ቅድመ-ሁኔታዎችን የሚያስቀምጥ ሕግ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸው እንደ ምስክሩ እና ጠቋሚው ሁኔታ ሊደረጉለት የሚገቡ የጥበቃ አይነቶችንም አካቶ የወጣ ሕግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ይህንን ላለፊት 11 ዓመታት በአገልግሎት ላይ የቆየውን ሕግ ለማሻሻል የሚያስችል ጥናት በማድረግ ከተቋሙ የምስክሮች ጥበቃ፣ ከሙስና ወንጀል ጉዳዮች እና ከተደራጁ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቶች፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና ከስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማቀፍ የማሻሻያ ሕግ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡
ለመሆኑ ህጉን ማሻሻል ለምን አስፈለገ ስንል ወ/ሮ ውበት ጋሻውን ጠይቀናቸዋል፡፡ ዳይሬክተሯ በምላሻቸው አዋጁን ለማሻሻል በምክንያነት ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ አዋጁ ምስክሮች እና ጠቋዎች ፍጹም የተለያዩ ሆነው ሳለ ሁለቱንም ቀላቅሎ የሚደነግግ በመሆኑ እንደየ ሰዎች ሚና ተገቢውን ጥበቃ ለመስጠት የሚያስችል አልነበረም፤ በተለይም ምስክርነት በባህሪው ጥቆማ ከመስጠት ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ከባድ በመሆኑ ይህንኑ ከግምት ባስገባ መልኩ መቀረጽ ስላለበት ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አክለውም ህጉ ጥቆማ መስጠትን ከወንጀል ተግባር ጋር ብቻ አዛምዶ የሚመለከት በመሆኑ በፍትሃ ብሄር እና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ጥቆማ የሚሰጡ ሰዎችን የማያበረታታ ሲሆን ይህም አጥፊዎችን በማስቀጣት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ መከላከልን መሠረት ያደረገ ስራ ለመሥራት እድል የሚፈጥር አልነበረም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዋጁ ላይ ስለ ስጋት ምርመራ የሚያወራ ድንጋጌ ባለመኖሩ ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ያሉባቸውን የስጋት ደረጃ ለመመርመር በሚደረግ ጥረት ውስጥ ባለሙያ ሊከተለው የሚገባ ወጥ መርህ ባለመኖሩ ስራ በራሱ ፈታኝ ሆኖ እንዲቆይ አድርጎት እንደነበር ከዳይሬክተሯ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እኚህን እና ሌሎች የአዋጁን ክፍሎች ከፈረምናቸው የአለም ዐቀፍ ስምምነቶች፣ ከሌሎች ሀገራት ልምዶች እና ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የማሻሻያ ስራው እንደሚሰራ ተብራቷል፡፡
የረቂቅ ቡድኑ አባላትም የሕግ ማሻሻያ ረቂቅ ዝግጅቱን በከፍተኛ ትኩረት በማርቀቅ እስከ በጀት ዓመቱ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ የመጀመሪያውን የተሟላ ረቂቅ አጠናቆ ለውይይት ዝግጁ እንደሚደርጉ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይም የሚመለከታቸው አካላት የሚሳተፉበት የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮች ተዘጋጅተው በረቂቁ ላይ ውይይት እንደሚደረግም ታውቋል፡፡
በረቂ ዝግጅቱ ላይ ሙያዊ የማማከር እና ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ስራውን እያገዘ የሚገኘው በተባበሩት መንግስታት የአደገኛ ወንጀል እና ዕጽ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ድርጅት UNODC የወንጀል መከላከል እና የወንጀል ፍትሕ ጉዳዮች ሃላፊ የሆኑት ሉዊዝ ፖርታስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጁ ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ለማሻሻል ማሰቡን በመግለጽ ሙያዊ ድጋፍ እንድናደርግ በጠየቀን መሠረት የህጉን አለም አቀፋዊ ባህሪ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመነሳት የተለያዩ ምክክሮችን ስናደርግ የቆየን ሲሆን የረቂቅ ስራው ከመጀመሩ በፊትም ከፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮች እና ባለሙያዎች ጋር የተለያዩ ምክክሮችን ስናደርግ ነው የቆየነው ብለዋል፡፡
በረቂቅ ዝግጅቱ ውስጥ ሊካተቱ የሚገቡ ፍሬ ነገሮችን በተመለከተ የመጨረሻው ውሳኔ የሚወሰነው በመንግሥት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ በኩል በማሻሻያ ረቂቅ ዝግጅቱ ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ያልናቸውን ጉዳዮች በሙሉ በማንሳት ድጋፍ እየሰጠን እንገኛለን ያሉት ሀላፊዋ አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር ህጉን ለሕግ አውጪው አካል አቅርቦ እስኪያጸድቅ ድረስ ተገቢውን ድጋፍ እያደረግን እንቆያለን፤ መንግሥት በማንኛውም ሁኔታ ከተቋማችን የሚፈልገውን ድጋፍ ለማድረግ ተቋማችን ዝግጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡