የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር በአፋርና አማራ ክልሎች በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የፍትህ ተቋማት እና ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ባዘጋጀው የመነሻ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ

Discussion on the Initial Plan to Support Justice Institutions and Victims Affected by the Conflict in Afar and Amhara Regions

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በአፋርና አማራ ክልሎች በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የፍትሕ ተቋማት እና ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ባዘጋጀው የመነሻ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት አካሄደ፡፡

በውይይት መድረኩ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አቶ አለምአንተ አግደው እንደሚታወቀው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ በፍትሕ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል:: በመሆኑም መንግሥት እንዚህን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ፍትሕ ሚኒስቴርም ተቋማቱን መልሶ በማቋቋሙ ረገድ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

በክልሎቹ ጉዳት የደረሰባቸው የፍትሕ ተቋማትን ችግር በአጭር ጊዜ ተፈትቶ ወደ ስራ ካልገቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እንዲሁም የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅምም በማስከበር በኩል ትልቅ ማነቆ ያስከትላልም ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ፍትሕ ሚኒስቴር ከአመራሮችና ከሰራተኞች ጋር በመወያየት በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች ከደሞዝ ልገሳ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች መደረጋቸውን አውስተው ነገር ግን ድጋፉ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ሲነጻጸር በቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች እንዴት እናግዝ፤ ጉዳት የደረሰባቸው የፍትሕ ተቋማቱን በምን መልኩ እናቋቁም የሚለውን የመነሻ ዕቅድ አቅደን እንዴት በጋራ እንደምንሰራ ለመወያየት ሀሳቡን ልናጋራችሁ ወደናል፤ ከእናንተም ብዙ የሚጠበቅ መሆኑን አውቃችሁ በዚሁ ልክ ለማገዝ እና አብሮ ለመሥራት ተገቢው ተሳትፎ እንደምታደርጉ ተስፋ አደርጋለው ብለዋል፡፡

የክቡር ሚኒስትር ዴዔታውን ንግግር ተከትሎ በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈቲያ ሰይድ የመነሻ ዕቅዱን ለመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን የዕቅዱ ዋና ዓላማም በጦርነቱ የወደሙትን የፍትሕ ተቋማት መገልገያ ቢሮ እና መሳሪያዎች ሁሉን አቀፍ በሆነ አግባብ በመደገፍ ወደነበሩበት ሁኔታ በመመለስ የፍትሕ ስርዓቱን የተሻለ ማድረግና የዜጎችን ክብርና ደኅንነት ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው በግብ ደረጃም በሁለቱ ክልሎች የተጎዱ ዜጎችን በተለያየ የድጋፍ ማዕቀፍ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳይገቡ መከላከል እንዲሁም በሁለቱ ክልሎች ላይ የወደሙ የፍትሕ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የፍትሕ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በመነሻ ዕቅዱ በሁለቱም ክልሎች በፍትሕ ተቋማት ላይ የደረሰ የንብረት ውድመት የተመላከተ ሲሆን በቢሮ ሕንጻዎች፣ ጠረቤዛ እና ወንበሮች ፣ ኮምፒውተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ ፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ እስታብላይዘር፣ እና ዲጂታል ካሜራዎች የሚገኙበት ሲሆን የፍትሕ ተቋማቱ ስራቸውን በጥራት ለማከናወን እነዚህ ግብዓቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገልጾ ባለድርሻ አካላትም ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እነዚህን ድጋፎች እንዲያደርጉና ተቋማቱ ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመለሱ በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡በመጨረሻም በመድረኩ የተለያዩ ሀሳብና አስተያቶች የተነሱ ሲሆን በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራሮች ምን መምሰል እንዳለባቸውና በምን አግባብ በትብብር ድጋፉ መደረግ አለበት በሚለው ሀሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ የቀጣይ አቅጣጫዎች ተቀምጠው የዕለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Afar • Amhara
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች