በውይይት መድረኩ በረቂቅ ደንቡ ውስጥ የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱን ሥልጣንና ተግባር የሚመለከተዉን ክፍል ያቀረቡት በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ፈትህያ ሰይድ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 35/1/ መሠረት የተቋቋመዉ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ፅ/ቤት በርካታ ተቋማትን በማስተባበር ከፍልሰት አስተዳደር አንፃር ያሉ ስራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እንዲመሩ በማድረግ በኩል ኃላፊነት እንደተሰጠዉ ገልፀዋል፡፡
ፅ/ቤቱ ፍልሰት ነክ የሆኑ ጥናቶችን ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በማካሄድ በጥናት የተገኙ ግኝቶችን ጥቅም ላይ የሚያዉል ሲሆን በተጨማሪም ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የፍልሰት የመረጃ ቋት ከማደራጀት በዘለለ በክልሎች የትብብር ጥምረቶች እንዲደራጁ ድጋፍ ማድረግና ሌሎች በርካታ ሀላፊነቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ አክለውም የብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ አባል የሆኑ 14 የመንግሥት ተቋማትን በማስተባበር በፍልሰት ጉዳዮች በአገራችን እንደ ተጠሪ በመሆን እንደሚሰራም ሀላፊዋ አብራርተዋል፡፡
ቀጥሎም የፍልሰት የተጎጅዎችን ፈንድ አስተዳደርና አጠቃቀም የሚመለከተዉን የረቂቅ ደንቡ ክፍል በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ በላይሁን ይርጋ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን በሰዉ የመነገድ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰዉን ለስራ ወደውጭ ሀገር መላክ ወንጀል ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የገቢ ምንጩ ከመንግሥት በጀት፣ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ከሚወረሱ ንብረቶችና የገንዘብ መቀጮዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚገኙ ልገሳዎችና ርዳታዎች መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡
የፈንዱ ዓላማም ለተጎጂዎች ህክምና፣ ለስነ ልቦናና የሕግ ምክር፣ ለትራንስፖርት፣ ለተጎጂዎች ቁሳዊ ርዳታና መሰል አገልግሎቶች ለማዋል መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተር ጀነራሉ የፈንድ አጠቃቀሙን በሚመለከት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣዉ ደንብ የሚወሰን ስለመሆኑ በአዋጅ 1178/2012 ተደንግጎ እንደነበርም ገልፀዋል፡፡
የተጎጅዎችን ፈንድ አስተዳደርና አጠቃቀም በቦርድ የሚመራ ሲሆን ቦርዱም የፈንዱን አስተዳደርና ስራዎች በበላይነት እንደሚመራና እንደሚያስተዳድር የተገለፀ ሲሆን የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ፅ/ቤቱም የፈንድ አስተዳደር ፅ/ቤት ሆኖ እንደሚሰራም በረቂቅ ደንቡ ተካቷል፡፡
በመጨረሻም በዉይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በረቂቅ ደንቡ ቢካተቱና ቢስተካከሉ ያሏቸዉን አስተያየቶቻቸውን የሰጡ ሲህን የግልፅነት ጥያቄዎችን አንስተዉ ሰፋ ያለ ዉይይት ከተካሄደ በኋላ በመድረክ መሪዎቹ አማካኝነት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዉ ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡