የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በትራንስፎርሜሽን ትግበራ እቅዱ ተግባራዊ እያደረጋቸው ከሚገኙ የለውጥ ስራዎች አንዱ በሆነው በአማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች፣ ማለትም በባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች ፣ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት እና በግልግል ዳኝነት ላይ ለሁለት ቀናት የሚቆይ የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ማካሔድ ጀምሯል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዓለምአንተ አግደው በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱ አምዶች መካከል አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ይገኝበታል ያሉት ክቡር ፕሬዝዳንቱ፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎችን ከመደበኛው የፍርድ ሂደት ጋር በማስተሳሰር ወይም ራሳቸውን በቻለ መንገድ ስራ ላይ በማዋል በአለም ላይ የተለመደ አሠራር ሲሆን ይህም የመደበኛውን የፍትሕ ስርዓት ጫና በመቀነስ የዳኝነትና አጠቃላይ ፍትሕ ስርዓቱን የተቀላጠፈ በማድረግና ውጤታማነቱን በመጨመር የፍትሕ ተገልጋዩን እርካታ በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋ፡፡
ክቡር ፕሬዝዳንቱ አክለውም እነዚህ አማራጭ መንገዶች ከቅልጥፍና እና የፍትሕ አገልግሎት ውጤታማነት ከማሳደግ ባሻገር በትክክል እውነትን በማውጣት እንዲሁም ቁርሾዎች እና በደሎች በትክክል እንዲያሽሩ እና ጉዳቶች እንዲጠገኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ገልፀው፣ መድረኩ ዓላማ ያደረገው ክልሉ በየአካባቢው ያለውን የዳበረ የግጭት አፈታት ሥርዓት እና ቱባ ባህል ከአለማቀፍና አገር አቀፍ ተሞክሮዎች አንፃር በማየት በክልሉ እንዴት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል የሚለውን ለመምከር እንደሆነ አመላተዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን በበኩላቸው ለመድረኩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት የቁልፍ መልእክት ሀገራችን በጀመረችው የሕግ ማሻሻያዎች እና የተቋም ግንባታ እንቅስቃሴዎች ምንም እንኳን አዎንታዊ ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም ባለፉት አምስትና ስድስት አመታት የተከናወኑ ስራዎችን ስንገመግም አሁንም ካለው ከህዝቡ ፍላጎትና ከህብረተሰቡ ጥያቄ አንጻር ከፍተኛ ስራዎችን መሥራት እንደሚገባን በጥናትና ምርምር ለመገንዘብ ችለናል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ክልሉ ያለበት ነባራዊ ሁነት የሚታወቅ ቢሆንም በከፍተኛ ትጋትና ስራ የ3 ዓመት ሀገርአቀፍ እና ክልል አቀፍ የሆነ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በመቀበልና በተጨባጭ ሁኔታና ፍላጎት እንዲሁም ቅድመ ጥናትን በማድረግ እና በማስተሳሰር አንድ ዓመት ተኩል ላይ ስራዎችን በመሥራት ከፍተኛ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንዳለ የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከአምዶቹ መካከል አንዱ የሆነውን የባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት እና በባህላዊ መንገድ ግጭትን የመፍታት ዘዴን አስመልክቶ ለመወያየት ብሎም ክልሉ በባህላዊ መንገድ ግጭቶችን ከመፍታት አኳያ ያለውን ልምድ ለመቀመር መድረኩ መዘጋጀቱ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ገልፀው ለቀጣይ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በቆይታቸው ወቅት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት አገልግሎቱን ምቹ ፣ ቀልጣፋ፣ የተደራጀ እና ዘመናዊ የስራ ከባቢ ለመፍጠር የጀመረውን የሕንጻ እድሳት፣ እንዲሁም በውስጡ ያሉ አዳዲስ ማሻሻያዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
መድረኩ በዛሬ ውሎው የኦሮሚያ ክልል የባህላዊ የግጭት አፈታት የዳሰሳ ጥናትን፣ ማኅበረሰብን መሠረት ያደረገ ፍትሕ በኢትዮጵያ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ሚና፣የኦሮሚያ እና የሲዳማ ክልል የባህል ፍርድ ቤቶች ተሞክሮ፣ የአማራ ክልል ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሽምግልና ስርአቶች ጥናት እንዲሁም የክልሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መነሻ ረቂቅ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃንን፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ደሴ ጥላሁንን ጨምሮ ፣ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ፣ የአማራ ክልል የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ፣ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎች ፣የሀይማኖት አባቶች፣የዘርፉ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡