በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ከ1 ሚሊዮን 967 ሺ ብር በላይ የሚያወጣ የአፈር ማዳበሪያን እያጓጓዙ እያሉ በተያዙት ተከሳሾች ላይ ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን መገልገል እና የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ማጓጓዝ ወንጀል ክስ መሰረተባቸው፡፡
በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ ደቻሳ አየነዉ፣ 2ኛ ተከሳሽ አደም ጀማል፣ 3ኛ ፀጋዘአብ ተክሌ፣ 4ኛ ሃሚድ ጋሻዉ፣ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ሁለት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
1ኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የዉጭ ሀገር ስሪት የሆኑ ብዛቱ በቁምጣ 900፣ በኩንታል 450፣ የዋጋ ግምቱ ብር 1 ሚሊየን 967 ሺ 850 ብር እና የቀረጥና ታክስ መጠኑ ደግሞ ብር 72 ሺ 259.14 ብር የሆነ ኤን ፒ ኤስ(NPS) የተባለዉን የአፈር ማዳበሪያ ምንም ዓይነት የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመበት ኮንትሮባንድ ሆኖ ሳለ፤ ዕቃዉ በህጋዊ መንገድ ገብቶ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ የተረከቡ ለማስመሰል በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ የምርት ማሳደጊያዎች ማስረከቢያ ሰነድ የወጪ ማዘዣ ቁጥር እና ቀን ተገልፆ በሐሰት የተዘጋጁ የምርት ማሳደጊያዎች ማስረከቢያ ሰነዶችን በመያዝ በሁለት ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪ ላይ በተጫነዉ ጌሾ ስር ደብቀዉ በመጫን 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች አሽከርካሪ በመሆን 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ ረዳት በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዉስጥ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በሚወስደዉ መንገድ ላይ በጋራ በመሆን እያጓጓዙ እያሉ በተደረገዉ ክትትል በቀን 15/05/2016 ዓ.ም ከቀኑ በግምት 06፡00 ሰዓት ሲል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የካ ክፍለ ከተማ እስራኤል ኤምባሲ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ሲያጓጉዙ የተያዙ በመሆናቸዉ በፈፀሙት ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በተመሳሳይ 2ኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ሲሆን ተከሳሾች የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ያልተፈፀመባቸዉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸዉ ከላይ በ1ኛ ክስ ዉስጥ በተገለፀዉ ሁኔታ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች አሽከርካሪ በመሆን 2ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች ደግሞ ረዳት በመሆን ብዛቱ በቁምጣ 900፣ በኩንታል 450፣ የዋጋ ግምቱ ብር 1 ሚሊዮን 967 ሺ 850 ብር የቀረጥና ታክስ መጠኑ ደግሞ 72 ሺ 259.14 ብር የሆነ ኤን ፒ ኤስ(NPS) የተባለዉን የአፈር ማዳበሪያ በጋራ በመሆን እያጓጓዙ እያሉ በተደረገዉ ክትትል የተያዙ በመሆኑ ተከሳሾች የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በማጓጓዝ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን ተከሳሾች ክሱ ደርሷቸው መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅና ክስ ለመስማት ለየካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡