በቀለ ጉርሜ የተባለው ተከሳሽ ሰውን ለመግደል በማሰብ ሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ሲሆን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 አያት ጨፌ አካባቢ ተከሳሽ ጨለማን ተገን በማድረግ ነውረኝነቱን እና ጨካኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ በያዘው እስታር ሽጉጥ ሟች አሸብር ኃይሉን ከኋላ የግራ ትክሻው እና ወገቡ ላይ ተኩሶ በመምታት ሟች ከመሳሪያው በተተኮሰበት የጥይት እርሳስ ጉዳት ደርሶበት በእለቱ ህይወቱ አልፏል፡፡
በመሆኑም በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡