ሰፋው ሸሪፍ ሳቢር የተባለው ተከሳሽ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 8፡10 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ቦሌ ጉምሩክ ካርጎ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ሟች ብርሃነ ተ/ሚካኤልን ሀያ ሁለት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወደ መኖሪያ ቤቱ ለመሄድ ተከሳሽ የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጠው 300 ብር ተስማምተው ተከሳሹም በላዳ መኪና እያሽከረከረ የሟች ቤት በር ላይ ሲደርሱ ሟች ከመኪናው ወርዶ ቤት ገብቶ ገንዘብ ይዞ በመምጣት ተከሳሽ ለሰጠው የታክሲ አገልግሎት በስምምነታቸው ላይ 100 ብር በመጨመር 400 ብር ይከፍለዋል፡፡
ከከፈለ በኋላ ሟች ተከሳሽን ስልክ እንቀያየር ሲለው ተከሳሽ እኔ ስልክ ቁጥሬን ልፃፍልህ በማለት ንብረትነቱ የሟች የሆነውን የዋጋ ግምቱ 14 ሺ ብር የሆነን ሳምሰንግ ጋላክሲ A03 ተንቀሳቃሽ ስልክ ከተቀበለው በኋላ ስልኩን ለመውሰድ እንዲሚቸው ሟች መኪናው ላይ በሾፌሩ በኩል ተደግፎ ቆሞ እያለ ተከሳሽ መኪናውን በከፍተኛ ፍጥነት መንጭቆ በማስነሳት ስልኩን ይዞ ሲሄድ ሟች ኮብልስቶን መንገድ ላይ በመውደቁ በራስ ቅሉ፣ ደረቱ እና ሆዱ ላይ በርካታ ጉዳት ደርሶበት ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ተከሳሽም ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ተንቀሳቃሽ ስልኩን የዋጋ ድርድር በማድረግ 7 ሺ 500 ብር ሽጦት ተከሳሹ በክትትል የተያዘ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የለኝም በማለት በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ15 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡