ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የፈጸመው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ ተቀጣ

Defendant Involved in Illegal Trafficking of Firearms Sentenced to Rigorous Imprisonment and Fine

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ካሳሁን አግማስ በተባለው ግለሰብ ላይ ፈጽሟል ባለው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ወንጀል የካቲት 22/6/2014 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩልዩ የወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሒድ ነበር፡፡

ተከሳሽ በ2012 ዓ.ም የወጣውን የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4(1) እና አንቀጽ 22(3) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያመላክተው ተከሳሽ በሕግ የፀና ፈቃድ ሳይኖረው 20,630 ፍሬ የክላሽ ጥይት፤ 260 የብሬን ጥይት፤ አንድ የስናይፐር ጠብመንጃ፤ 1የብሬን ጥይት መያዣ ዝናር ወይም ሰንሰለት፤ በሚያሽከረክረዉ ኤፍ ኤስ አር ተሸከርካሪ በድብቅ የተሰራ ቦታ ወይም ሻግ ዉስጥ ጭኖ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ አቅጣጫ እሽከረከረ እያለ በቀን 19/05/2014 ከምሽቱ በግምት 5፡00 ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ በአ/ከ/ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታዉ መሳለምያ አከባቢ ሲደርስ እጅ ከፍንጅ ከጦር መሳርያዎቹ ጋር የተያዘ በመሆኑ በፈጸመው የጦር መሳሪያ ማዘዋወር ወንጀል ተከሷል፡፡

የተከሳሽን የዋስትና መብት በተመለከተ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ በዋስትና ቢወጣ የሚጣልበትን ቅጣት በመፍራት ሊጠፋ ይችላል ብሎ በመከራከሩ ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ ሲከታተል ቆይቷል፡፡

ተከሳሽ በፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ከተነበበለት በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲል ክዶ የተከራከረ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ የወንጀሉን መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮች ግንቦት16/2014 ዓ.ም አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያሰማ ሲሆን የሰነድ ማስረጃዎችም አያይዞ አቅርቧል፡፡

ፍርድቤቱም የምስክሮቹን መሰማት ተከትሎ ተከሳሽን ተከላከል ሲል ሀምሌ 20/2014ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ብይን የሰጠ ሲሆን በዚህም መሠረት ተከሳሽ ነሀሴ 10/2014 ዓ.ም 4 የመከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ ቢያሰማም ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥቅምት 9ቀን/2015 ዓ.ም በተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ ጥፋተኛ ነህ በማለት የቅጣት ማቅለያ ካለው በጹሁፍ እንዲያቀርብ ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

ህዳር 2ቀን/03/2015 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩልዩ የወንጀል ችሎት በእለቱ የተሰየመ ሲሆን በዚህም መሠረት ተከሻሽ ያቀረባቸውን 5 የቅጣት ማቅለያዎች በመቀበል የቅጣቱን መነሻ እርከን ከ29 ወደ 24 ዝቅ በማድረግ በ6ዓመት ከ6ወር ጽኑ እስራትና በ2000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡

Tagged Under: ababa • addis • addis ababa • amharic legal terminology • arms • arms trafficking • conviction • court • Criminal Code • district • federal • Federal High Court • fine • firearms • firearms control • high • illegal • imprisonment • lideta • lideta district court • oromia • oromia region • region • Sentencing • trafficking
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች