መንገድ ዳር ቆማ ታክሲ በመጠበቅ ላይ ያለችን ግለሰብ በባለሶስት እግር ተሽከርካሪ አሳፍረው በመውሰድ ንብረቶቿን የወሰዱና ህይወቷ እንዲያልፍ ያደረጉ ወንጀለኞች በእስራት ተቀጡ

Criminals Who Kidnapped and Killed a Woman Waiting for a Taxi, Stealing Her Belongings, Sentenced to Prison

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ በረከት ብርሃኑ፣ 2ኛ ዮናስ ካሳ፣ 3ኛ ዳግም ውብሸት የተባሉ ሶስት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ሰላም ፍሬ ጤና ጣቢያ አካባቢ ተከሳሾች በባለሶስት እግር ተሸከርካሪ በመጓዝ ላይ እያሉ ወ/ሮ እጸገነት አንተነህ የተባለች ግለሰብ መንገድ ዳር ቆማ ታክሲ በመጠበቅ ላይ እያለች ትሄጃለሽ ብለው በመጠየቅ አሳፍረው ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን መንገድ ላይ ይወስዷታል፡፡

ቀጥሎም ከላይ በተጠቀሰው ቦታ ሲደርሱ በአካባቢው ሰው አለመኖሩን ካረጋገጡ በኋላ በወቅቱ የያዘችውን ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቻቸው 3ኛ ተከሳሽ አንገቷን በእጁ አንቆ ሲይዛት ስትንፈራገጥ፣ 2ኛ ተከሳሽ እግሯን በመያዝ ጄ ፋይፍ ሳምሰንግ ሞባይል ግምቱ 7 ሺ ብር፣ ጥቁር ተንጠልጣይ ቦርሳ፣ ሁለት ጃኬት እና ሁለት ሱሪ ግምታቸው 2 ሺ 450 ብር፣ የብር የአንገት ሀብልና የጣት ቀለበት ግምቱ 400 ብር፣ የሆኑ ንብረቶቿን ከወሰዱባት በኋላ ከባጃጁ ውስጥ አውርደው መንገድ ላይ ጥለዋት ይሰወራሉ፡፡

የወሰዱትን ንብረትንም ሸጠው ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋል እና ግለሰቧም በእጅ አንገቷን በመታነቋ እና በራሷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ህይወቷ በዚሁ እለት እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ሁሉም ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ከዚህ ቀደም ወንጀለኞቹ በ14 ዓመት ተቀጥተዉ የነበረ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠይቆበት በድጋሜ በተሻሻለ ዉሳኔ መሠረት 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በ20 ዓመት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ16 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡

Tagged Under: 1996 criminal code • accomplices • addis ababa • Aggravated Robbery • aqaqi qality • auto-rickshaw • capital punishment • code • conviction • court • criminal • Criminal Code • district • federal • Federal High Court • felony • high • Homicide • Kidnapping • lideta • lideta district • Murder • prison • prison sentence • property confiscation • Robbery • sentence • Theft
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች