ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በሟች ፋሲካ ተሾመ ላይ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ዙሪያ እየተካሄደ ያለው የምርመራ ሥራ ተጠናክሮ የቀጠለ ስለመሆኑ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጎአ ገልጸዋል፡፡
ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ጥቆማ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን በፍትሕ ሚንስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ከልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጋር በጋራ በመሆን የምርመራ ቡድን በማዋቀርና የምርመራ እቅድ በማዘጋጀት ምርመራ የተጀመረ ሲሆን በምርመራው የሰው ምስክርና የተጠርጣሪዋን የእምነት ክህደት ቃል የመቀበል ስራ መሰራቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በቅድመ ምርመራ ሂደት በተሰበሰበ ማስረጃ መሠረት ዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 10፡45 ሰዓት ሲሆን በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ክልል ልዩ ቦታው አስኮ አዲስ ሰፈር ሊዝ መንደር እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ የቤት ሠራተኛ የሆነችው ተጠርጣሪ አበቡ ሙላት አሰሪዋን ሟች ፋሲካ ተሾመን አንገታቸው ስር በቢላዋ በማረድ፤ የግራ ደረታቸው እና የቀኝ ጆሮ ግንድ ላይ በመውጋት እንዲሁም የኃላ ጭንቅላታቸውን በብረት ዘነዘና በመፈንከት ብዙ ደም ፈሷቸው ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጋ ከቤት ተሰውራለች በማለት ጥቆማ ከቀረበበት ዕለት አንስቶ የተለያዩ የምርመራ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ተጠርጣሪን ከተሰወረችበት አፈላልጎ የመያዝ ስራው የተከናወነ ሲሆን ማስረጃ የማሰባሰብ ተግባሩም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል አቶ ሲሳይ።
በቀጣይም በምርመራው መሰራት ያለባቸውን የምርመራ ስራዎች በፍጥነት በማከናወን የምርመራ መዝገቡ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገቢው ውሳኔ ይሰጣል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡