የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ላይ ምክክር ተካሄደ

Consultation Held on the Federal Administrative Procedure Proclamation and Transitional Justice Policy

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ እና የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈጉበዔ፣ የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ የኮሚቴ አባላት፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ የዲሞክራስ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትን በመወከል እንዲገኙ ጥሪ የተደረገላቸው ኃላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ሥነ ሥርዓት አዋጅ አፈፃፀምን በተመለከተ በአዋጁ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከመወጣት ጎን ለጎን በአዋጁ ተፈፃሚነት ላይ የክትትል ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ ተቋሙ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን አዘጋጅቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቦ መጽደቁን አመላክተዋል፡፡

አያይዘው አዋጁ እና ፖሊሲው በመንግሥት አካላት ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር እንዲሁም ተቋሙ በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ም\ቤቱ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ያግዘው ዘንድ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም\ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ቁርሾዎች እንዲጠገኑ እና ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር እንዲሳካ የተሟላ የሽግግር ፍትሕ መተግበር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሀገራዊ አውዱ እንደሚያመላክት ገልፀው አስተዳደራዊ ፍትሕ ከወንጀል እና ፍትሐ ብሔራዊ ክርክሮች በላይ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ወይም እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር የፍትሕ ዘርፍ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካየች ምክር ቤት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚሰጠው የድጋፍ፣ የቁጥጥር እና የክትትል አይነቶችን ለመለየት ያስችለው ዘንድ ም\ቤቱ በሽግግር ፍትሕ እና በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጁ ዙሪያ ውይይት መደረጉ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ የፌደራል አስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ አጠቃላይ ዳሰሳ እና የአተገባበር ሁኔታ፣ በአተገባበር ወቅት የታዩ ክፍተቶች እና ምክንያታቸው፣ በፍርድ ቤት እየታዩ ባሉ የክለሳ ጥያቄዎች ላይ እየታዩ ያሉ የውሳኔ አሰጣጥ እና አመራር ዝንባሌዎች፣ የአዋጁ አፈፃፀም ላይ ለሚደረገው የክትትል ስራ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ስለሚኖርው የቅንጅት ስራ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የመጀመሪያውን ገለፃ ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ይዘት እና ዳሰሳ፣ አስፈላጊነት፣ የሽግግር ፍትሕ ዓላማ እና መርሆዎች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በክቡር ሚኒስትሩ የቀረበ ሲሆን ከግጭት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ በሚደረግ ሽግግር ከሽግግሩ በፊት በደረሱ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች የተሟላ መፍትሄ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል፡፡

በቀረቡት በሁለቱም ገለፃዎች ላይ በክቡር ሚኒስትሩ እና በክቡር አፈጉባኤው አወያይነት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይት መድረኩ በተሳታፊዎች በርካታ ሃሳብ እና አስተያየቶች የተሠጡ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ከመድረኩ ምላሽ እና ማብራሪያዎች ተሰጥቷል፡፡ ዉይይቱ በGIZ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን በመድረኩ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ ገንቢ ሃሳቦች መነሳታቸው ተመላክቷል፡፡

Tagged Under: Accountability administrative administrative justice civil liberties constitutionalism democratic institutions federal Federal Administrative Procedure Proclamation GIZ house house of peoples’ representatives human Human Rights Violations Justice Legal Reform peoples' Policy procedure proclamation Representatives Rights rule Rule of Law speaker of the house transitional transitional justice Transitional Justice Policy violations
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች