በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዳሬክቶሬት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል እንዲሁም ህብረተሰቡ ለፍትሕ ስርዓት አጋዥ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ አስመልክቶ የውይይት መድረክ በትላንትናው ዕለት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የዳይሬክቶሬቱ የሕዝብ አደረጃጀት አባላት የሆኑና በአዲስ አበባ በ11ዱ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተገኝተዋል፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ በረከት ማሞ እንዳሉት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ብሎም ወንጀል ፈፃሚዎች ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በየጊዜው ውስብስብ እየሆኑ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ የወንጀል ድርጊቱ የሚፈፀሙባቸውን አካባቢዎች በመለየት፣ ወንጀል ሲፈፀምም ጥቆማ በማቅረብ እና ምስክር በመሆን ብሎም ተጎጂዎችን በመደገፍ ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ በመርዳት፤ አጥፊዎች ሳይቀጡ እንዳይቀሩ በማድረግ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በበጀት አመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት ውስጥ በስራ ክፍሉ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን በማካተት የተዘጋጀውን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ፀጋ የማነ ባደረጉት ገለፃ ዳሬክቶሬቱ በፌደራል እንዲሁም በአዲስ አበባ፣ ድሬደዋ እና ሀዋሳ በሚገኙ ምድብ ጽ/ቤቶች ደረጃ በጠቅላላ 1195 መዛግብት ለምርመራ የቀረቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወንጀል ፈፃሚዎችንም ከ10 ዓመት እስከ ሞት ቅጣት በሚደርስ ፍርድ እንዲቀጡ ለማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አክለውም ዳሬክቶሬቱ በአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ መስተዳድሮች ውስጥ በሚገኙ የተቀናጀ የፍትሕ እንክብካቤ ማዕከላት አማካኝነት ለ900 ባለጉዳዮች አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በሌላም በኩል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ በሴቶችና ሕፃናት ላይ በስፋት ወንጀል እየተፈፀመባቸው የሚገኙ አካባቢዎች ላይ የፍትሕ አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በጥምረት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘም በመድረኩ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት በስራ ላይ የሚገኙ ህጎችን ከህገመንግስቱ እና ከዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች አንፃር በማንሳት ሰፋ ያለ ሙያዊ ማብራሪያ ለተሳታፊዎች ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻ በዕለቱ የተነሱ ጉዳዮችን በማስመልከት ከተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ በቀጣይነት የሕዝብ አደረጃጀቶች እንዲሁም መላው የህብረተሰቡ ክፍል ለፍትሕ ስርዓት አጋዥ በመሆን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል፡፡