በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በኃላፊነት ከተረከበው የባንኩ ገንዘብ ላይ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በመውሰድ ለግል ጥቅሙ ባዋለው የዳሽን ባንክ ጎፋ ቅርንጫፍ ገንዘብ ያዥ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሰረተበት፡፡
ክሱ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን ተከሳሽ ታስሮ ችሎት ቀርቧል
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው አሸናፊ ተስፋዬ ደምሴ የተባለው ተከሳሽ የማይገባውን ብልጽግና ለራሱ ለማግኘት በማሰብ በዳሽን ባንክ አክሲዮን ማህበር ጎፋ ቅርንጫፍ በከፍተኛ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ገንዘብ ያዥ የስራ መደብ ላይ ተቀጥሮ በሚሰራበት ወቅት በቅርንጫፍ ባንኮች በተደረገ ድንገተኛ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራ መገኘት ከነበረበት ገንዘብ ውስጥ 1 ሚሊዮን 150 ሺ 731 ብር ጉድለት የተገኘ በመሆኑ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31/2/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው የከባድ እምነት ማጉደል የሙስና ወንጀል ተከሷል።
ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ የደረሰው ሲሆን የተከሳሽን መቃወሚያ ለመቀበልና የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ መርመርምሮ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተጥቷል፡፡