በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት የአዳማ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በ2015 የበጀት ዓመት ከኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበር የወንጀል ተግባራት ክርክር ከተደረገባቸዉ 151 የጉሙሩክና የታክስ ወንጀሎች መዛግብት ዉስጥ 101 መዛግብት ዉሳኔ ማግኘታቸዉን ገልጿል፡፡
ከእነዚህ ዉሳኔ ካገኙ መዛግብት ዉስጥ ሁለት ሚሊዬን አራት መቶ ሰባ ዘጠኝ ሺ አንድ መቶ ሰላሳ ሁለት ብር (2,479,132) የገንዘብ መቀጮ የተሰበሰበ ሲሆን አራት ሚሊዬን አራት መቶ ሀምሳ ሺ (4,450,000) ብር ደግሞ በዋስትና የተያዘ ገንዘብ ገቢ ሆኗል፡፡
ዉሳኔ ካገኙ መዛግብት ዉስጥ ለአብነት ስንመለከት ከጉምሩክ የወንጀል ድርጊቶች አንጻር በእነ ዘላለም አለማሁ መዝገብ በተካተቱ 2 ሰዎች የምግብ ፐሮገራም (WFP) የጥራጥሬ እህል ላይ የቅሸባ ወንጀል በመፈጸም የጉምሩክ ሕግን በመተላለፋቸዉ በቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራዉ ተጠናቆ ክስ ተመስርቶ ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻላቸዉ የአዳማ ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ዉሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን በዚሁ መሠረትም እያንዳንዳቸዉ በ8 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡
በተያያዘ ከታክስ ወንጀል ጋር በተገናኘ ከታዩ መዛግብት ዉስጥም የአዳማ ገቢዎች ቅ/ጽ/ቤት ባካሄደዉ ኦፕሬሽን የተጭበረበረ ደረሰኞችን ማዘጋጀት፣ መሸጥ፣ ማሰራጨት እና ያለ ግብይት ደረሰኝ መስጠት የወንጀል ድርጊት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ ተይዘዉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣርዎችን ፍ/ቤት አቅርቦ የዐቃቤ ሕግና የመከላከያ ማስረጃዎች ተሰምተዉ ለዉሳኔ ለ05/12/2015 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡
የአዳማ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በዋናነት የታክስና የጉሙሩክ ሕግን ተላልፈዉ በሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢዉን ቅጣት እንዲያገኙ ለማስቻል ታስቦ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በገቢዎች ሚኒስቴር፣ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በፌዴራል ፖሊስ የጋራ ስምምነት መሠረት ተከፍቶ ስራዉን እየሰራ ይገኛል፡፡