ሮባ አበበ የተባለው ተከሳሽ በተለያ 3 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን በአንደኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ መጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 5፡25 ሰዓት ሲሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ጎፋ የመጀመሪያ ደ/ት/ት ቤት የመምህራን ማረፊያ ክፍል ውስጥ ሟች ናኔሳ በሻዳ የተባለውን ግለሰብ ከሚስቴ ጋር ግንኙነት አለህ በማለት ቂም በመያዝ እጀታው የእንጨት የሆነ ቢላ ለዚሁ የወንጀል ድርጊት ቀደም ብሎ ገዝቶ ካስቀመጠበት ቁም ሳጥን ውስጥ በማውጣት ሟችን በስለት በመውጋት ጉዳት በመድረሱ ምክንያት ህይወቱ ያለፈ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል፤ እና በተመሳሳይ በ2ኛ እና በ3ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ በያዘው ስለት በመውጋት በሁለት ግለሰቦች ላይ ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡