ከግል መኖሪያ ቤቶች በር ገንጥሎ በመግባት ስርቆት የፈፀመው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ

Accused Sentenced to Hard Labor for Breaking into Private Residences and Committing Theft

ወንድሙ ሞላ የተባለው ተከሳሽ በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ በሁለት ክሶች የተከሰሰ ሲሆን በአንደኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት በማሰብ ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 7፡15 ሰዓት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ኮተቤ ሰላም ዳቦ ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት የሳሎን በር ገንጠሎ በመግባት ያልተያዘው ግብረአበሩ ፌሮ ብረት ይዞ ሲያስፈራራ፣ ተከሳሹ ደግሞ ሽጉጥ ይዞ ባትሪ እያበራ እንዳትንቀሳቀሱ በማለት የግል ተበዳይን ግንባሩ ላይ በመደቀን እንደሚተኩስበት በማስፈራራት፣ ሌላኛው ግብረአበር ደግሞ የጣውላ እንጨት እንደ መሳሪያ አድርጎ በመያዝ አንድን ግለሰብ እንዳትበላሽ በማለት በማስፈራራት ለግል ተበዳይ እርዳታ እንዳይሰጥ በማድረግ ጥሬ ብር፣ የተለያዩ ሞባይሎችንና የጣት የወርቅ ቀለበት አጠቃላይ ዋጋቸው 82 ሺ ብር የሚገመት ንብረት በመውሰድ ተከሷል፡፡

በተመሳሳይ በ2ኛ ክሱ ላይም ተከሳሽ ከላይ በ1ኛ ክስ በተገለፀው ቦታና ሰዓት እንዲሁም አኳኋን መሠረት ከሌላ ተበዳይ መኖሪያ ቤት ገብተው በማስፈራራት የተለያዩ 10 ሺ 200 ብር የሚገመቱ ንብረቶችን የወሰዱ በመሆኑ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀመው የውንብድና ወንጀል ክስ አቅርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኗል፡፡

Tagged Under: Court Verdict • Criminal Sentencing • Robbery • Violent crime
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች