በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ሕግ 1ኛ የኢንሹራንስ ኤጀንት በሆነው ሰለሞን ታቦር ፀጋ ስላሴ 2ኛ የራይድ ሾፌር በሆነው ታምራት ተክሌ እሸቴ ፈጽመዋል ባለው በከባድ አታላይነት እንዲሁም በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት በዛሬው ዕለት 4 ተደራራቢ ክሶችን መስርቶ አቅርቧል፡፡
ተከሳሾች የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/ 2007 አንቀጽ 32 (2) እና (3) ፣ አንቀጽ 23 (2)(ሀ) እና 3 እንዲሁም በ1996 ዓ/ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ጠቅሷል፡፡
የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱን በተመለከተም በ1ኛ የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾች ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋለው ግብረአበራቸው የአምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ቃሜን ስም (ማንነት) የተዘጋጀውን ሀሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም፤ እራሱን አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በማድረግ ለሁለቱም ተከሳሾች ልዩ ውክልና ከሰጣቸው በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ሁለት ተሽከርካሪዎችን በአምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ስም በሐሰት የተዘጋጀ የባለንብረትነት መግለጫ በማቅረብ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለሁለቱም ተሽከርካሪዎች አረቦን የገዛ ሲሆን፣
ሁለተኛ ተከሳሽ በበኩሉ 8 ሰው የሚይዝ ቶዬታ V8 ተሸከርካሪ ሀምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በባሌ ሮቤ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው መስቀል ስጋ ቤት ፊት ለፊት ተሽከርካሪውን ካቆምኩበት ተሰረኩኝ በማለት ሀምሌ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በተጭበረበረ መንገድ ያገኘውን ውክልና በመጠቀም ለሮቤ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ እና ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሮቤ ዲስትሪክት ሀሰተኛ ሪፖርት እና የምስክርነት ቃል በመስጠት ሁለቱም ተከሳሾች በተጭበረበረ መንገድ ያገኙትን ውክልና በመጠቀም ከፍተኛ ጉዳት በሚያደርስ መልኩ የV8 መኪና ግምት 17,994,000 (አስራ ሰባት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ዘጠና አራት ሺህ ብር) በአስቸኳይ የካሳ ክፍያ እንዲፈጽም በሚል በተደጋጋሚ የካሳ ክፍያ ለመውሰድ ድርጅቱን የጠየቁ በመሆኑ በፈጸሙት ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ተከሰዋል።
ዐቃቤ ሕግ በ2ኛ እና 3ኛ የክስ መዝገቡ ላይ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ክሱን የመሰረተ ሲሆን ተከሳሹ በሙያው የኢንሹራንስ ኤጀንት መሆኑን ያለአግባብ በመጠቀም አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የተባሉ ግለሰብን ማንነት ተጠቅሞ ሀሰተኛ ሰነድ ባዘጋጀው እና ለጊዜው ካልተያዘው ግብረአበር ጋር በመሆን አምባሳደሩ ምንም በማያውቁበት ሁኔታ ልዩ ውክልና በመውሰድ የአምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ያልሆነውን V8 ተሽከርካሪ በተጭበረበረ መንገድ የመድን ሽፋን በማስገኘት የካሳ ጥያቄ ለማቅረብ በማሰብ፤ ተሽከርካሪው በአምባሳደሩ ስም እንደሚገኝ የሚያሳይ ሊብሬ በማቅረብ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት እኤአ ከሚያዚያ 27 ቀን 2022 እስከ ሚያዚያ 26 ቀን 2023 ዓ/ም ድረስ የሚሸፍን የመድን ሽፋን ድርጅቱ እንዲሰጥ በግል ተበዳይ ስም በሐሰት በከፈተው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር የአረቦን ¬¬ክፍያ ገቢ በማድረግ በተጨማሪም ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር በአንደኛ ክስ በተጠቀሰው አግባብ ከድርጅቱ የካሳ ክፍያ የጠየቁ በመሆኑ እንዲሁም በ3ኛ ክስ ላይም በተመሳሳይ ሀሰተኛ ሊብሬ በመገልገል የመድን ሽፋን በአምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ስም በመግባት ተከሳሹ በፈጸመው በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ 2ኛ ተከሳሽ ሀሰተኛ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ በመገልገል በፈጸመው በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀልም ክስ መስርቶበታል፡፡
ተከሳሾች ክሱ ደርሷቸው በግል ጠበቃ እንከራከር ወይስ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ይመድብልን የሚለውን ጉዳይ ከቤተሰብ ጋር ተማክረን እንቅረብ ብለው ለችሎቱ ጥያቄያቸውን ባቀረቡት መሠረት ችሎቱም ውጤቱን ለመጠባበቅ ለመጋቢት 4/2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡