የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የተቋም ግንባታ የሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ከጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር የአስተዳደር ፍትሕ ላይ የሚደረጉ ትብብሮች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተዉ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ጀርመን የፌዴራል መንግሥት አወቃቀርን የሚከተሉ አገራት እንደመሆናቸዉ መጠን የሚከተሏቸዉ ሥርዓቶችም በዛዉ ልክ ተመሳሳይነት ያላቸዉ መሆናቸዉ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ አንጻር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ማርቀቅ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ከጀርመን ልምድ የተወሰደ መሆኑን፣ ይህም በተለይ ክልሎች ይህን ሕግ በሚያወጡበት ወቅት ትልቅ እገዛ እንዳደረገ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕግ ከማውጣት ባለፈ ሕጉ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የተሻለ አተገባበር እንዲኖር ለማድረግ በቀጣይ ሊከናወኑ ስለሚገባቸው ተግባራትና ለዚህም ከጀርመን ጋር ሊደረግ ስለታሰበው የልምድ ልዉዉጥ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡
በተያያዘም የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በፌዴራል ደረጃ ፀድቆ ትግበራ ላይ እንዳለና አብዛኞቹ ክልሎችም በተመሳሳይ ሕጉን የማርቀቅና የማፅደቅ ስራ ማከናወናቸዉ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይ በክልሎች በሚፈለገው ልክ እንዲተገበር ለማድረግ አስፈላጊው የአቅም ግንባታ ተግባር ሊከናወን እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጰያ መንግሥት በፍትሕ ሴክተሩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በሚያከናዉናቸዉ ሌሎች ተግባራት ዙሪያም ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የወንጀልና ፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት እና ሌሎች ተግባራትን አስመልክቶ በቀጣይ መሰል ዉይይቶችን በማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡