በፌደራል እና በክልሎች በሚገኙ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛ ተቋማት በሰዎች የመነገድ እና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት ያለመ ሀገራዊ የምክክር መደረክ እየተካሄደ ነው

National Consultative Forum Held to Integrate Human Trafficking and Migrant Smuggling Crimes into the Curriculum of Federal and Regional Justice Organs Training Institutions

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፌደራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በሀገራችን ከሰዉ ልጅ መሠረታዊ የመንቀሳቀስና የመዘዋወር ህገመንግስታዊ መብቶች ጋር በሚጣረስ መልኩ የሚፈጸሙ በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እንዲሁም ተያያዥ ወንጀሎችን ለመከላከል ብሎም የተጠናከረ የፍልሰት አስተዳደርን ለመዘርጋት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቁመው የአዋጅ ቁጥር 1178/2012 መዉጣትን ተከትሎ በፌደራል ደረጃ በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ያካተተ ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረትና የጥምረቱ ጽ/ቤት መቋቋሙን ገልፀዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለፃ ወንጀሎችን ቀድሞ ከመከላከልና አጥፊዎችን አስተማሪ የሆነ ቅጣት በማስቀጣት ረገድ ጠንካራ የፍትሕ ተቋማት እና የሰለጠኑ የፍትሕ ባለሙያዎች የሚያስፈለጉ ከመሆኑም በተጨማሪ በተናጠል ከሚሰሩ ስራዎች ባለፈ የሁሉንም የሥልጠና ተቋማት ቀጥተኛ ተሳትፎና ጠንካራ ቅንጅታዊ ስራዎች መሥራትን ይጠይቃል።

አምባሳደሩ አያይዘውም ሥልጠናዎች የካበተ ልምድ ባላቸዉ የፌዴራልና የክልል የሥልጠና ተቋማት ሞጁል ተዘጋጅቶ በካሪኩለም ዉስጥ ተካተዉ እንዲሰጡ ማድረግ ሥልጠናዎቹ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲደርሱ ከማስቻሉም ባሻገር ተደራሽነቱን በማስፋት የቅድመ ስራና ድህረ ስራ ሰልጣኞች ቀጣይነት ባለዉ መልኩ በወንጀሎቹ ዙሪያ በቂና ወቅታዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው በፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢኒስቲትዩት፣ በአንዳንድ ክልሎች የፍትሕ አካላት የሥልጠና ተቋማት እንዲሁም በፌዴራል ፖሊስ ዩንቨርሲቲ የተሰሩትና በመሰራት ላይ ያሉት በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ተያያዥ ወንጀሎችን በሥልጠና የማካተት ስራዎች የሚበረታቱና በሁሉም ክልሎች ተጠናክረዉ ሊቀጥሉ የሚገቡ መሆናቸዉን ገልፀው ይህ አገራዊ ምክክር ከተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ ዕጽና ወንጀሎች መከላከያ ቢሮ (UNODC) ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም ይህ የምክክር መድረክ የፍልሰት ጉዳዮች በተለይም በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች በፍትሕና ሕግ የማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩቶች ራሱን የቻለ ካሪኩለምና የማስተማሪያ ሞጁል ተዘጋጅቶለት እንዲሰጥ በሚደረግበት ጉዳይ ላይ የሚመክር እና መልካም ተሞክሮዎችን የምንጋራበትና የምናዳብርበት እንዲሁም የጋራ አቅጣጫ በመያዝ ለቀጣይ ስራዎች የምንዘጋጅበት ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፌደራል ፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘካርያስ ኤርኬሎ የህገ ወጥ ሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን ድንበር ማሻገር ወንጀል ስርዓተ ሥልጠናን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያዎችን ተሰጥቷል፡፡

መድረኩን ፍትሕ ሚኒስቴር እና UNODC ያዘጋጁት ሲሆን የክልል የፍትሕና ሕግ ኢንስቲቲዩቶች ኃላፊዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈውበታል፤ ክልሎችም ተሞክሮዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተጠቁሟል፡፡ ሃገራዊ ምክክሩ ህዳር 11 እና 12 በአዲስ አበባ ኔክሰስ ሆቴል እተካሄደ ይገኛል፡፡

Tagged Under: Border Control • Capacity Building • counter-trafficking • Crime • cross-border • Cross-Border Crime • curriculum • curriculum development • development • federal • federal justice and law institute • human • Human Trafficking • institute • Justice • law • law enforcement training • legal framework • migrant • Migrant Smuggling • National • national consultative forum • Policy Development • Smuggling • trafficking • Training • UNODC
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች