በሰው የመነገድ ወንጀል በመከላከልና በተጎጂ ሕፃናት ጥበቃ ረገድ በክልሎች መካከል ያለውን የትብብር እና የቅብብሎሽ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ

Consultative Forum Held to Strengthen Inter-Regional Cooperation and Referral Systems for Combating Human Trafficking and Protecting Child Victims

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽሕፈት ቤት ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ፣ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) እና ከዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት (Save the Children) ጋር በመተባበር በሰው መነገድን ለመከላከል፣ ተጎጂዎችን ለመለየትና የቅብብሎሽ ሥርዓትን ለማጠናከር ያለመ የልምድ ልውውጥ እና የምክክር መድረክ ከሚያዚያ 20 እስከ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል፡፡

መድረኩ በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ የሰዎች መነገድ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ሲሆን፣ ተጎጂዎችን በትክክል በመለየት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸውና ከማኅበረሰቡ ጋር መልሶ እስከማዋሃድ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ በክልሎችና በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን የተቀናጀ አሰራርና የቅብብሎሽ ሥርዓት ውጤታማ ለማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ ላይ እንደተመለከተው፣ በተለይም መነሻቸውን ከአማራ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በማድረግ ዋና መዳረሻቸውን አዲስ አበባ ባደረጉ የሕፃናት ዝውውሮች ላይ የሚስተዋለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሰው መነገድ ወንጀል ለመግታት፣ የተቀናጀ የጋራ አሠራር መዘርጋት የግድ እንደሚል ተጠቁሟል። ለዚህም በፌዴራል፣ በክልልና በከተማ አስተዳደሮች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለተጎጂዎችና ተጋላጭ ሕፃናቱ ተገቢውን ጥበቃና ምላሽ መስጠት የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡

በመድረኩ ቆይታም ዓለም አቀፍና አገራዊ የፍልሰት አስተዳደር የሕግ፣ ተቋማዊና የትብብር ማዕቀፎች፣ የወንጀል መከላከል ተቋማዊ አደረጃጀቶች፣ የብሔራዊ የቅብብሎሽ ሥርዓት አተገባበር፣ የተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የሚያተኩሩ የመነሻ ሀሳቦች ቀርበው ሰፊ ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የሰዎች መነገድ ወንጀል ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ወይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ተሳታፊ ክልሎችም ወንጀሉን ለመከላከልና ተጎጂዎችን ለመጠበቅ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትንና ያካበቷቸውን ተሞክሮዎች ለሌሎች አካፍለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው በዚህ የምክክር መድረክ፣ ወደፊት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው ውይይት ተደርጎባቸው የጋራ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፣ በተለይም የቅብብሎሽ ሥርዓቱን ወደ ተግባር መቀየር፣ የአገር ውስጥ ፍልሰትና በሰው መነገድ ወንጀሎች መነሻ ምክንያቶችን መፍታትና የተጠናከረ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ የቅብብሎሽ ሥርዓት አተገባበርን ማሻሻል እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

Tagged Under: african charter on the rights and welfare of the child child children combating combating human trafficking consultative Cooperation Forum human Human Trafficking ict iom operation per pro ratio referral referral system region Regional Regional Cooperation save the children system systems traffic trafficking victim victims
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች