ዓለም ዓቀፉ በሰው የመነገድ ቀን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት በየዓመቱ እ.ኤ.አ ሐምሌ 30 ተክብሮ ይዉላል፡፡ ዘንድሮም ፍትሕ ሚኒስቴር ከዓለምዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት ጋር በመተባበር በዓለም ለ12ኛ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ” በሰው የመነገድ ወንጀል የተደራጀ ወንጀል ነው፤ የሰዎች ብዝበዛንም እናስቁም ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተከብሮ ውሏል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ቀኑን ማክበራችን እንደ አገር በሰው የመነገድ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ያለንን ቁርጠኝነትና አጋርነት ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሳወቅና ነው ያሉ ሲሆን የፍልሰተኞችን ሰብዓዊ መብቶች በማስጠበቅ እና የአገርን ደኅንነት በማረጋገጥ የፍልሰትን መልካም እድሎች ወደ አገራዊ ልማት መቀየርና መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጽዋል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታዉ አክለዉም አገራችን በተባበሩት መንግሥታት የተደራጁ ድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የወጡትን ሁለት የፓሌርሞ ፕሮቶኮሎች ተቀብላ እና ባላት ሕገ መንግሥት በማጽደቋ የማስፈጸም ኃላፊነቱ በየትኛዉም የአስተዳደር እርከን ላይ የሚገኙ የፌደራል እና የክልል ሕግ አዉጪ፤የዳኝነት እና የአስፈጻሚ አካላት ላይ ተጥሏል ብለዋል፡፡
ወንጀሉን የመከላከል እና የመቆጣጠር ጉዳይ የብዙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ቅንጅትና ትብብር የሚፈልግ መሆኑን በመረዳት በክቡር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ም/ቤት ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ሚኒስትር ዲኤታዉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለምዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት የኢትዮጵያ ሚሽን ኃላፊ ተወካይ ሚስተር ሳሻ ንላቡ በበኩላቸዉ አሁን ላይ እየታየ ያለው በሰው የመነገድ ወንጀል አፈጻጸሙ ዓለምዓቀፋዊ በመሆኑ ችግሮቹን ለመፍታት በአገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ የሆነ ትብብር እና ቅንጅት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በፕሮግራሙ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር፤ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብረሀም አያሌው በፕሮግራሙ ላይ ለተገኙ ተሳታፊዎች በብሔራዊ ደረጃ ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለመግታት እና ተጎጂዎችን ለመርዳት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ የተጠናከረ የስደት ፖሊሲ አለመኖር፤ በፌደራል እና ክልል መንግሥታት መካከል ያለው ትብብር እና ጥምረት ደካማ መሆን፤ ለስደት ገፊ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን በበቂ ሁኔታ መለየት አለመቻሉ፤በቂ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖር፤ ግልጽ የሆነ የጠረፍ አካባቢ የግንኙነት ፖሊሲ አለመኖር፤ ተበዳዮችን መሠረት ያደረገ የምርመራ ሥርዓት እና የተጠናከረ የተጎጆዎች ልየታ አለመኖሩ በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልፀዋል፡፡
ዕለቱ ሲታሰብ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን አስከፊነት የሚያሳዩ ፊልሞች ለታዳሚዎች የቀረቡ ሲሆን ሕገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በፍትሕ ሚኒስቴር የተዘጋጀዉን የጥቆማ መስጫ 8797ን የማስተዋወቅ ሥራ የተሠራ ሲሆን የፓናል ዉይይትም ተደርጓል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ፤ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች እና የሚዲያ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የዓለምዓቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ህገወጥ የሰዎች ዝዉዉርን ለመካለከል እና ተጎጂዎችን ለመርዳት እስካሁን ላደረገዉ ያላሰለሰ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡