በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን አስመልክቶ ለሚደረግ የፋይናንስ ምርመራ የሚካሄድበት የአሰራር ስርአት ይፋ ተደረገ

A Procedure for Financial Investigation into Human Trafficking and Illegal Migrant Smuggling Offenses was Unveiled

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ እና የፉይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በጋራ በመሆን ያዘጋጁት እና በተሻሻለው የፍልሰት አስተዳደር መርሃግብር በአውሮፓ ህብረት እና የጀርመን ፌደራል መንግሥት ሲቪፓል በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀ የአሠራር ሥርዓት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የስራ ማስጀመሪያ መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ሴክሬታርያት ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሐም አያሌው በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እንዲሁም ህገወጥ የውጭ አገር የስራ ስምሪት የሰብዓዊ መብትና የደኅንነት ስጋት ከመሆናቸው ባሻገር ያልተገባ የገንዘብ ወይም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት የሚፈፀሙ ወንጀሎች መሆናቸውን ገልፀው አገራችንም የእነዚህ ወንጀሎች ተጠቂ መሆኗንና በዚህም በዜጎች አካል ህይወትና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እያጋለጣቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም ይህንን ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተው በዋናነት የመከላከል፣ሕግ ማስከበር፣ የተጎጅዎች ጥበቃ እና አጋርነት የሚሉ ቁልፍ ስትራቴጅዎች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙና በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ የሕግ ማስከበር የስራ ቡድን ተቋቁሞ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም ገልፀዋል።

በዋናነት እነዚህ ወንጀሎች የሚፈፀሙት ያልተገባ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት በመሆኑ የወንጀል ፍሬዎች ላይ ተገቢውን ምርመራና ክትትል ማድረግ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ተከትሎ ትይዩ የፋይናንስና የንብረት ምርመራዎችን በማሻሻል የወንጀል ፍሬዎችን በመውረስ የወንጀል አትራፊነትን እንዲቀንስ በማድረግ በኩል የአሠራር ስርአቱ እጅግ አጋዥ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት የገለፁት ሃላፊው ለዚህም የገንዘብና ቴክኒካል ድጋፍ ላደረጉት ለሲቪፓል እና ለአዘጋጅ ኮሚቴው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሲቪፓል ቢኤም ኤም ክልላዊ አስተባባሪና ቡድን መሪ ማርኮ ቡፍ በበኩላቸው መደበኛ ባልሆነው ፍልሰት በተለይም ለህገወጥ ደላሎች የሚከፈል ገንዘብ እጅግ ውስብስብና በአለማችን ያሉ አገራት ተጠቂ እየሆኑበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ይህንን ተከትሎ በኢትዮጵያ በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን አስመልክቶ የፋይናንስ ምርመራ የሚካሄድበት መደበኛ የአሠራር ሥርዓት መዘጋጀቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እጅጉን አጋዥ እንደሚሆን ገልፀው ስርአቱን በማዘጋጀት ሂደት የነበረው የጋራ ቅንጅትና የጋራ አስተዋፅኦ በአሠራር ስርአቱ ትግበራ ሂደትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

በፋይናንስ ምርመራ ጥቅም ላይ የሚውል ቅደም ተከተሎችን የጠበቁ ሂደቶችን ማስተዋወቅ የአሰራሩ አስፈላጊነት ሲሆን በሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ተያያዥ ወንጀሎች ጎን ለጎን በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ከማቅረብ ወንጀል ጋር አብሮ ለማጣራት በሚደረጉ የምርመራ፣ክስ የማቅረብና ንብረት የማስመለስ ሂደቶች ውስጥ የፋይናንስ ምርመራን እንደ ዋና ፍሬነገር በመውሰድ በእነዚህ ወንጀሎች ረገድ የሚኖርን ምርመራ ማገዝን ዋና ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱ ሰነዱ በቀረበበት ወቅት ተገልጿል።

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች