የብሔራዊ ምክር ቤት እና የትብብር ጥምረት የአስተዳደርና አደረጃጀት መመሪያዎች ተዘጋጅተው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የፍልሰት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባሉበት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል፣ የከተማ መስተዳድሮችና የክልል ባለድርሻ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ፀድቀዋል፡፡
መመሪያዎቹን አቅርበው ገለፃ ያደረጉት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ ሲሆኑ በዚህም የመመሪያዎቹን መነሻ፣ የትብብር ቅንጅት አደረጃጀቶች፣ በጥናት የተለዩ ችግሮች፣ የመመሪያዎቹ የዝግጅት ሂደትና ይዘታቸውን ያካተተ ሰነድ አቅርበው ሰፊ ገለፃ አድርገዋል፡፡
የፍልሰት ጉዳዮችን በሚመለከት በሰው መነገድ እና ሰዉን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሠረት ወንጀል መከላከል፣ ጥፋተኞችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ለተጎጂዎች ድጋፍ ማድረግና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም አገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ትብብርን ማጠናከር የሚሉት መርሆች ለመመሪያዎቹ የዝግጅት አምዶች መሆናቸውን ያወሱት ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው በዚህ አዋጅ መሠረት የተቋቋመውን ብሔራዊ ምክር ቤት፣ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት እና ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊነቶችን በዝርዝር አቅረበው ገለፃ አድርገዋል፡፡
መመሪያዎቹን ለማዘጋጀት በተደረገ ጥናት መሠረት የተገኙ ቸግሮችም ቀርበው ገለፃ የተደረገባቸው ሲሆን በዚህም ምክር ቤቱ የውስጥ አሠራርን የሚመለከት መመሪያ ያልተሟላለት መሆኑ፤ በትብብር ጥምረቱ በኩል እንደዚሁ የጥምረቱ መመሪያ 563/2012 ከወጣ በኋላ አዳዲስ ሕጎች መውጣታቸው፣ አዋጁ በክልሎች ያለውን ተፈፃሚነት በአግባቡ ለመከታተልና ለመደገፍ አለመቻሉ፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በየጊዜው ከሀገር የሚወጡ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የተመላሽ ዜጎች ቁጥር መጨመር፣ ወቅታዊና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታው ተለዋዋጭ መሆንና ጫና ማሳደር የሚሉና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች በጥናት የተለዩ ችግሮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ሚንስትር ዴኤታው አክለውም በጥናት የተለዩ ችግሮችን መነሻ በማድረግ መመሪያዎቹን ለማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 መሠረት የነበረውን ሂደት ጠቅሰው፤ በዚህም የብሔራዊ ምክር ቤቱ የአሠራር መመሪያ ጠቅላላ ድንጋጌዎች፤ የምክር ቤቱ አባላት አሠራር ከብሔራዊ ጥምረትና ከክልል ምክር ቤቶች ጋር ስላለው ግንኙነት፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ሕጎች መተግባር ማሻሻል በሚሉ ሶስት አበይት ክፍሎች የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል አራት አበይት ክፍሎችን አካቶ የተዘጋጀው የብሔራዊ የትብብር ጥምረት የውስጥ አደረጃጀትና አሠራር መመሪያን ጠቅላላ ድንጋጌዎች፤ የጥምረቱ አደረጃጀት የስራ ቡድኖች ተግባር፣ ኃላፊነትና ተጠሪነት የአሠራር ሥርዓት፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች የተሻሩና ተፈፃሚነት የሌላቸው ሕጎች የመተግበር ግዴታ በሚል የተካተቱ ነጥቦችን በዝርዝር አቅርበው ገለፃ አድርገዋል፡፡ የቀረቡት መመሪዎችን አስመልክቶም የመድረኩ ተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያየቶችን አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የፍልሰት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፌዴራልና ከክልል ለመጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መመሪያዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡