በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ፣ማርቀቅ ፣ማረምና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ አዲስ ጌትነት የስራ ክፍሉን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሕግ የተሰጠውን በፌዴራል መንግስቱ የሚወጡ ሕጎችን ጥራት የማረጋገጥ ኃላፊነት መነሻ በማድረግ ከተለያዩ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የቀረቡ 98 ረቂቅ ህጎችን (15 ረቂቅ አዋጆች፣ 33 ረቂቅ ደንቦች፣ 54 ረቂቅ መመሪያዎች እና 1 ረቂቅ ስትራቴጂ) ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ ምግስት፣ ሀገራችን ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ከሌሎች የሀገራችን ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች አንፃር በማየት የሕግ ምርመራ/እርማት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝብ እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማረጋገጥ አንዱ የሕግ ጥራት ማረጋገጫ መንገድ በመሆኑ ከተለመደው የገጽ ለገጽ ውይይት እና በጽሁፍ አስተያየት ከመቀበል ባለፈ ሰዎች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው በሚዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች ላይ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ ሀሳብና አስተያየታቸውን መቀበል የሚያስችል በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የኦንላይን ምክክርና አስተያየት መስጫ ፖርታል የማልማት ስራ ቀደም ብሎ ተጀምሮ ሲሰራ የነበረ መሆኑን አንስተው በፖርታሉ ላይ ግብዓት የማሰባሰብ እና የማሳደግ ስራ የተከናወነ መሆኑን፣ በፖርታሉ ዙሪያ ለባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን፣ ፖርታሉን ወደትግበራ ለማስገባት ቀሪ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨመሪም የህጎችን ጥራት የማረጋገጥ ስራ የሚያግዝ የሕግ ምክር እና ማረም ረቂቅ ማኑዋል መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ህጎች ተፈፃሚነትን ከማሳደግ አንጻር በአስተዳደር ተቋማት የተዘጋጁ መመሪያዎች 100% መመዝገብና በድረ-ገጽ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ታቅዶ በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን መስፈርት አሟልተው ከተለያዩ አስተዳደር ተቋማት የተላኩ 21 መመሪያዎች ተመዝግበው በተቋሙ ድረ-ገጽ ላይ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ መደረጉን ሀላፊው በማብራሪያቸው ገልፀዋል።
አቶ አዲስ በገለፃቸው የፍትሕ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በተሟላ ሥርዓት ለመምራት እንዲቻል ለማድረግ በባለፈው በጀት ዓመት ተጀምሮ የነበረውን ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በተሰበሰበው ግብዓት መሠረት እንዲዳብር መደረጉን አውስተው የረቂቅ አዋጁን ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ በመሰራት ላይ መሆኑን፣ የአዋጁ ማሰፈፀሚያ ረቂቅ መመሪያ (የአገልግሎት ተጠቃሚዎች መለያ መስፈርቶችን ያካተተ ረቂቅ መመሪያ) እና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍያና ወጪዎች መወሰኛና ፈንድ አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከሌሎች ስራ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስፈፀሚያ 4 ህጎችን የመጀመሪያ ረቂቅ የማዘጋጀት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፤ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት መድብል/ኮድ የማዘጋጀት ስራ በቀጣይነት መከናወኑን አንስተዋል፡፡
ከጥናት አኳያ የፍትሐብሔር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ጥናት እና በወንጀል ቅጣት አወሳሰን ወጥነት ጥናት ሲደረግ የቆየ መሆኑን ያወሱት ሀላፊው ከዚህ በተጨማሪ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከያ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት መነሻ ጥናት በመከናወን ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
በ3 ረቂቆች መለትም በጤና አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ እና በመድሃኒት አቅራቢ ተቋም ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ላይ ለጤና ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ላይ ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ፣ የማበረታቻ ማዕቀፍ እና የትስስር ፈንድ ረቂቃ ደንብ ዝግጅት ላይ ለትምህርት ሚኒስቴር የረቂቅ ሕግ ዝግጅት ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል ኃላፊው።
ኃላፊው አያይዘውም ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በቀረቡ 29 ጉዳዮች ላይ የሕግ ምክር አገልግሎት መሰጠቱን አንስተው በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እነዚህና ሌሎች መሰል ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።