ከሐምሌ 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ሲካሄድ የነበረው 2ኛ ዙር የመካከለኛ አመራሮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
ስለሥልጠናው የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና የሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ሥልጠናዉ ቀደም ሲል በተደረገ ጥናት ላይ ተመስርቶ እየተሰጠ እንደሆነና በተለይ አሁን ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር የቀጣይ 5ዓመት የተቋሙን ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ በመሆኑና የሥልጠናው መሠጠት ለስትራቴጂው ዝግጅት በግብዓትነት ሊያገለግል ስለሚችል ዓላማዉ የግለሰቦችን አቅም ከማሳደግም በላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ሥልጠናዉ በዋናነት ትኩረት ያደረገዉ በስትራቴጂክ አመራር፤ ስትራቴጂክ ዕቅድ እና ለዉጥ አመራር ላይ ሲሆን በቀጣይ አመራሮቹ ያሉባቸዉን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችላቸዉን በቂ ግንዛቤ ለማግኘት እንደሚያግዛቸዉ ሚኒስትር ዲኤታዉ አያይዘዉ ገልጸዋል፡፡
ሥልጠናዉ ወቅቱን የጠበቀ እንደሆነ ያነሱት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታዉ በአሁኑ ወቅት የተቋሙን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማዘጋጀት የፍላጎት ዳሰሳ ተደርጎ እና ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ በመሆኑ እናንተም የራሳችሁን አስተዋጽኦ እንድታደረጉ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት በነበረዉ ቆይታ የሥልጠናዉ ተሳታፊዎች የቡድን ዉይይቶችን ያደረጉ ሲሆን ፍትሕ ሚኒስቴር በቀጣይ የሚያዘጋጀዉን የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ግብዓቶችንም እንዲሁ ማግኘት ተችሏል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ እና ለዉጥ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኖህ ታከለ በበኩላቸዉ የአገራችንን የፍትሕ ሥርዓት ለማሻሻል ድጋፍ ሲያደረግ የቆየዉን የአዉሮፓ ህብረት አመስግነዉ ባለፉት ዓመታት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያሉበትን የሎጂስቲክስ ችግሮችን ከመፍታት እና የሥልጠና ወጪዎችን ከመቻል ጎን ለጎን በለዉጥ አመራር እና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመለየት በሚደረጉ ጥናቶች ላይ ህብረቱ ላደረገዉ ያላሰለሰ ድጋፍ እዉቅና ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በሥልጠናዉ ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸዉን የሰጡ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በቆይታቸዉ በስትራቴጂክ አመራር፤ ስትራቴጂክ ዕቅድ እና ለዉጥ አመራር ላይ ከጽንሰ ሀሳቡ ጀምሮ እስከ አተገባበሩ በቂ እዉቀት ማግኘት እንደቻሉ እና በቀጣይም በሚመሩት የሥራ ክፍል ተጨባጭ ለዉጥ ለማምጣት እንደሚያግዛቸዉ ገልፀዋል፡፡ ሥልጠናው በቀጣይም ለ3ኛ ዙር እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡