በቅርብ ጊዜ ፍትሕ ሚኒስቴርን ለተቀላቀሉ ዐቃቤ ሕጎች በክረምት ልዩ መርሀ-ግብር የኢኮኖሚ ወንጀልን አስመልክቶ ከነሀሴ 27-30/2017 ዓ.ም የሚቆይ የሥራ ላይ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
በሥልጠና መድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር ወጣት ባለሙያዎችን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሥራ እያስገባና ለስራቸው አጋዥ የሆኑ የሥራ ላይ ሥልጠናዎች በመስጠት፤ ባለሙያዎቹ ከነባር ባለሙያዎች ልምድ እንዲቀስሙ እና ሥራቸውን በቀላሉ ቶሎ እንዲለምዱ ብሎም በሥራ ላይ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲያልፉ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ሥልጠናው የአሰራር ሥርዓቶች፣ ሕጎች እና ትርጉሞች ላይ በምን አይነት መልኩ ትምህርትና ልምድ መውሰድ እንደሚችሉ እንዲሁም ምን ዓይነት አፈጻጸሞች እንዳሉ ለሥልጣኞች ከማስገንዘብ በተጨማሪ፣ በሥራ ላይ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ስለሚያጋጥሙ ባለሙያዎችና ፈጻሚዎች ተገቢውን ዕውቀትና ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥልጠና መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ የሚሰጡ ሥልጠናዎች የቅድመ ሥልጠና እና የድህረ ሥልጠና መልመጃ እንደሚኖር እንዲሁም በውይይት ላይ ያተኮር ሥልጠና እንደሚሆን የተነሳ ሲሆን ለሥልጠና አጋዥ የሚሆኑ ሰነዶች እንዲሁ እንደሚዘጋጁ ተገልጿል፡፡