በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት የወንጀል ምርመራ ክስ አዘገጃጀት እና የክርክር ክህሎትን ለማጠናከር የሚያስችል ተግባር ተኮር የክረምት ሥልጠና በተቋሙ ሥር ለሚገኙ ዐቃቢያነ ሕጎች በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ሥልጠናዉ ለ6 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በ2015 እና 2016 ዓ.ም ተቋሙን የተቀላቀሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ዋነኛ ተሳተፊዎች ናቸዉ፡፡ ተመሳሳይ ሥልጠና በፍትሕ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንደተሰጠ የተገለጸ ሲሆን በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ዐቃብያነ ሕግ ሥራዎቻቸዉን ሲሠሩ ያጋጥሙ የነበሩ ክፍተቶች ተለይተዉ እና ሰነድ ተዘጋጅቶ የሚሰጥ ተግባር ተኮር ሥልጠና ነዉ፡፡
የወንጀል ምርመራ አጀማመርና ጠቅላላ ሂደት፤ዐቃቢያነ ሕጎች በምርመራ መዝገቦች ላይ የሚሰጧቸዉ ዉሳኔዎች፤የክስ አመሠራረት እና በክስ አመሠራረት እና ዉሳኔ አሰጣጥ ወቅት የሚያጋጥሙ አከራካሪ ጉዳዮች፤ የክስ እና የምስክር አሰማም ሥርዓት፤የመክፈቻ እና መዝጊያ ንግግሮች፤የቅጣት አስተያየቶች እና የይግባኝ ሥርዓት የሥልጠናዉ ዋነኛ የትኩረት ነጥቦች ናቸዉ፡፡
ሠልጣኞች በሥራ ወቅት ያጋጥሟቸዉ የነበሩ ችግሮችን እያነሱ በቡድን ሆነዉ የሚወያዩ ሲሆን በቀጣይ ለሥራቸዉ አጋዥ የሆኑ የልምድ ልዉዉጦች እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡