የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ለተጠሪ ተቋማቱ ማለትም ለሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት፣ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፣ለፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በአዋጅ ቁጥር 1183/2020 የወጣውን የአስተዳደር ስነ-ሥርአት ሕግን አስመልክቶ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን የአስተዳዳር ስነ-ሰርአት ህጉን በተቋማት በመተግበር መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው በንግግራቸው የምናገለግለውን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን አመኔታ ከፍ ለማድረግ፣ የሕዝብ አገልግሎትን ለማሳለጥ እንዲያስችል እንዲሁም አዋጁን አስመልክቶ ግልፀኝነትን ለተጠሪ ተቋሞቻችን ለመፍጠር እና የተቋማቱን አመራሮች ዕውቀትና ክህሎት ለማዳበር ይህ ሥልጠና መዘጋጀቱን አውስተዋል፡፡
ሥልጠናው በዋናነት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ህጉ ምንነት እና ጠቀሜታ፣ የአስተዳደር መመሪያ አወጣጥ ስነ-ስርዓት፣ የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት፣ የፍርድ ቤት ክለሳ እንዲሁም በህጉ የዜጎች መብት እና የአስፈፃሚ አካላት ግዴታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሥልጠናው በፍትሕ ሚኒስቴር ንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ እንዳልካቸው ወርቁ እና በዳሬክቶሬቱ ዐቃቤ ሕግ በአቶ መስፍን መኮንን ከታህሳስ ዐ9 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።