ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሙስናን መታገል በተግባር በሚል መሪ ቃል በሃገራችን ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ ሙስና ቀንን ከባለድርሻ አካላት፣ ከተጠሪ ተቋማት እና ከተቋሙ መካከለኛ አመራሮች ጋር የፓናል ውይይት በማድረግ በዛሬው እለት አክብሯል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በመልዕክታቸው ሙስናን ለመታገል ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ የፍትሕ ሚኒስቴር ሙስናን ከመታገል አንፃር ሰፊ የሆነ ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ አመራሮች እና ባለሙያዎች ከተሰጣቸው ኃላፊነት አንፃር ልዩ የሆነ የስነ-ምግባር ሁኔታን ተላብሶ መገኘትን ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የፍትሕ ሚኒስቴር ከስነ-ምግባር አንፃር የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት አቶ ዘላለም ፍቃዱ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ህጎችን በማስከበር የሕዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ተልዕኮ ያለው ተቋም መሆኑን በማውሳት ይህን ተልዕኮ ከመወጣት አንፃር ተቋሙ ባለፉት አራት ዓመታት ምርመራን ከመምራትና በጋራ ከማከናወን፤ ክስ መስርቶ በመከራከር እና የተመዘበረ የሕዝብ ሀብትን ከማስመለስ አንፃር የተለያዪ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ ዘላለም አክለውም ባለፉት ዓመታት ጉቦ እና የማይገባ ጥቅም በጠየቁ እና በተቀበሉ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞች፣ የታክስ ኦዲተሮች፣ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ህጎች፣ ፖሊሶችእና ሌሎች ስራ አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ ክሶች እንደቀረቡ ገለፀዋል፡፡
በሙስና ወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስን በተመለከተ 346,796,006.79 ብር፣ 11 ተሸከርካሪ፣ 2 መኖሪያ ቤቶች፣ 2,569 ካ.ሜ ቦታ እና 2 ቢሊየን ብር የሚገመቱ ከባድ ተሸከርካሪዎች እንደተወረሱ ሙስና ከመዋጋት አንፃር በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የተሰሩ ስራዎችን ባቀረቡበት ወቅት አብራርተዋል፡፡
ሃገራዊ የሆነውን የሙስና ችግር ለመቀነስ በፌደራል ደረጃ ሰባት አባላት ያሉት የጸረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የሚመራ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደተጀመረም አያይዘው ገልፀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም የሕግ ማዕቀፍ እና የተቋም ግንባታ ሪፎርሞች ሙስናን ከመታገል አንፃር ያላቸውን ፋይዳ የሕግ ጥናት ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል በሆኑት አቶ አዲስ ጌትነት ቀርቦ ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቆዎችም ሰፊ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው መንግሥት ሙስና ላይ በጣም የጠነከረ አቋም ነው ያለው፤ ለዚህ ማሳያም ተግባራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል መሃል ላይ ሃገሪቱ በነበረችበት ችግር ምክንያት መቀዛቀዝ የታየ ቢሆንም አሁን የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ አሁን ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች አሉ ይህን አጠንክሮ መቀጠል እያንዳንዳችን ሃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለም አንተ አክለውም የሙስና ወንጀል የተግባር ትግል ይፈልጋል፤ በመሆኑም ወንጀሎችን በመመርመር አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ እና የሕዝብ ሀብትን በማስመለስ ረገድ ሁሉም የተጣለብትን ኃላፊነት በተሻለ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም የጸረ-ሙስና ቀንን በፓናል ውይይቶች እንዳከበረ ይታወሳል፡፡