የተባበሩት መንግስታት የዕጽና ወንጀል ጽ/ቤት /UNODC/ ከአሜሪካና ከጃፓን ኤምባሲዎች ባገኘው ድጋፍ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ስር ለሚገኙት የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል እና ለምስክሮችና የወንጀል ጠቋሚዎች ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የማስፈጸም አቅማቸውን ለማጠናከርና ለማሳደግ የሚረዱ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ በዛሬው ዕለት አድርገዋል፡፡
በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጸጋ የተባበሩት መንግስታት የዕጽና ወንጀል ጽ/ቤት /UNODC/ ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ ከተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል እንዲሁም ከምስክሮች ጥበቃ ጋር ተያይዞ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ገልጸው በቅርቡም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጸመውን ጥፋት ለማጣራት ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ አድርገዋል ብለዋል፡፡
ከሥልጠናውም በተጨማሪ አቅምን በማገልበቱ በኩል የሎጀስቲክ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ተረድቶ UNODC፤ የሎጀስቲክስ ድጋፍ በማድረግ የሥልጠናውን ገቢርነት በማረጋገጡ እና ከዚህ ቀደምም ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት ለተደረገው ድጋፍ በሙሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል፡፡
ተቋማቱም ከዚህ ድጋፍ በተጨማሪ ሀገራችን በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ፣ሽብርተኝነትን፣ ህገ-ወጥ የዕጽ ዝውውር እና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት እንዲሁም ወንጀሉ ተፈጽሞ ሲገኝ አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ አኳያም የሚሰሩ የሕግ ማስከበር ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠሉ ረገድ እንዲሁም የምስክሮችና የጠቋሚዎችን ጥበቃ ለማጠናከር የሚሰሩ ስራዎችን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የዕጽና ወንጀል ጽ/ቤት /UNODC/ ለፍትሕ ሚኒስቴር የሚደረገውን የቁሳቁስ ድጋር በተቋማቱ ተወካዮችና በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው በኩል ርክክብ የተደረገ ሲሆን ቁሳቁሶቹም በአይነት ላፕቶፖች፣ዴስክቶፖች እንዲሁም ሶፋና ጠረቤዛዎች ይገኙበታል፡፡
ከርክክቡ በኋላ በተደረገው የሁለትዮሽ ውይይትም ተቋማቱ በቀጣይ ስለሚኖራቸው ቅንጅታዊ አሠራር የተነጋገሩ ሲሆን በሀገራችን በሰሜኑ ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ በአፋር፣በአማራና በትግራይ ክልሎች የተፈጸሙትን ወንጀሎች ለማጣራት ለተላከው የምርመራ ቡድን ምርመራው አለማቀፋዊ ስታንዳርድ እንዲኖረው ለማስቻል UNODC ከሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን(OHCHR)እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(EHRC) ጋር በመተባበር የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱን ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱ ሲሆን በቀጣይም የምርመራ ሰነዶችን ከማደራጀት ጋር በተያያዘ ለምርመራ ቡድኖቹ ሥልጠናዎች እንዲሰጡና ባሉባቸው የሎጂስቲክስ እጥረቶችም ተቋማቱ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበው እየተሻሻለ ያለውን የምስክሮችና የወንጀል ጠቋሚዎች አዋጅ ቁጥር 699/2003 የማሻሻል ስራውን UNODC በሙሉ አቅሙ በመደገፍ ረገድ ትልቅ ድርሻ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
ከUNODC የመጡት ተወካዮች በበኩላቸው በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ በተቋማቸው በኩል ክፍተቱን ለመሙላት ፍትሕ ሚኒስቴር የሚያቀርበው ጥያቄ ካለ አደራጅቶ እንዲያቀርብ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በሚቀርቡት ጥያቄዎች መሠረትም ክፍተቱን ለማስተካከል እና ማንኛውንም አገዛ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡በመጨረሻም አቶ ፍቃዱ ጸጋ UNODC በዚህ አግባብ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ ለውጥ እንዲያመጣ ፍላጎት ማሳየቱ በድጋሜ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረው እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍም እንደ ተቋምም የሚኖሩት የድጋፍ ጥያቄዎች ተጠናክረው እንደሚቀርቡ ገልጸው የእለቱ መርኃ-ግብር ተጠናቋል፡፡