በፍትሕ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ እና ታክስ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍርዴ ቸሩ እንደገለጹት በ2ዐ14 በጀት ዓመት እቅድ ግማሽ ዓመት 913 የምርመራ መዛግብት ለዐቃቤ ሕግ እንደቀረቡና ከነዚህም ውስጥ በ790 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሰጠ ገልጸው 123 መዛግብት ደግሞ በምርመራ ሂደት ላይ እንዳሉ እና በቀጣይ 3ኛ ሩብ ዓመት ውስጥ ውሳኔ የሚያገኙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም በፍርድ ቤት የነበረውን የመዛግብት ክርክር ውጤታማነት ሲገልጹ በግማሽ አመቱ 1019 መዛግብት ላይ በፍርድ ቤት ክርክር የተደረገ ሲሆን ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተላለፈባቸው በ210 መዛግብት 369 ተከሳሾች እንደሆኑና በ9 መዛግብት 19 ተከሳሾች በነጻ እንደተሰናበቱ ገልጸው ሌሎች መዝገቦች ግን በክርክር ሂደት ላይ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ በዚሁም መሠረት ዳይሬክቶሬቱ በግማሽ ዓመቱ የማስቀጣት ምጣኔው ከዕቅድ አንጻር ሲታይ 95.89 በመቶ ለማድረስ የተቻለ ሲሆን በተከሳሽ ብዛት የማስቀጣት ምጣኔም 95.1 በመቶ እንደሆነ እና በግማሽ አመቱ የማስቀጣት ምጣኔ በመዝገብም ይሁን በተከሳሽ ብዛት የተሻለ አፈጻፀም ማሳየቱን አቶ ፍርዴ ገልጸዋል።
ውሳኔ ከተሰጣቸው መዛግብት ውስጥ ሃያ ስምንት ተከሳሾች በከባድ ወንጀል ውሳኔ እንደተሰጣቸው የገለጹት ኃላፊው አራቱ መዝገቦች ተከሳሽ በሌለበት የተወሰኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ውሳኔ ከተላለፈባቸው መዝገቦች መካከል በማሳያነት የገለጹዋቸው በነ አላዛር መዝገብ 7 ሰዎች ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ መሸጥ እና በሀሰተኛ ደረሰኝ 300,000,000 (ሶስት መቶ ሚሊዮን) ብር ግብር እና ታክስ በመሰወር በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በመርዳትና በመተባበር እንዲሁም ኔት-ወርክ በመፍጠር ህገ ወጥ ደረሰኝ በማሰራት ጥፋተኝ ተብለው ሁሉም ተከሳሾች እያንዳዳቸው ከ3 ዓመት ከ3 ወር እስከ 12 ዓመት ጽኑ እስራት እና ከ25 ሺህ ብር እስከ 125 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ መቀጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
በእነብርሃን ኃይሌ መዝገብ በ8 ሰዎች ላይ ሀሰተኛ ማንነትና መታወቂያ፣ በሀሰተኛ አድራሻ ንግድ ፍቃድ በማውጣት ደረሰኝ መሸጥ፣ በኔት-ወርክ በመደራጀት ደረሰኝ በማሰራጨት ግብርና ታክስ መሰወር፣ ሀሰተኛ እና አሳሳች መግለጫ በማቅረብ ክስ ቀርቦባቸው ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን ከ7 እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እና ከ45 ሺህ ብር እስከ 300,000 ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
በእነ አባቢን ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማ በ6 ሰዎች ላይ ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ መሸጥ እና በሀሰተኛ ደረሰኝ 300,000,000 (ሶስት መቶ ሚሊዮን) ብር ግብር እና ታክስ በመሰወር በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በመርዳትና በመተባበር እንዲሁም ኔት-ዎርክ በመፍጠር ህገ-ወጥ ደረሰኝ በማሰራጨት ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ9 ዓመት እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራትና ከብር 750,000 እስከ 1,500,000 (አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡
በእነታደለ ንጉሴ መኪና አስመጪነት የንግድ ስራ በመሰማራት ሌሎች ግለሰቦች በቱሪስት መልክ ከቀረጥ ነጻ ያስገቡትን መኪና ቀረጥና ታክስ እንደተከፈለበት በማድረግ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥት ላይ ጉዳት በማድረስ፣ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ሀሰተኛ የግብይት ሰነድ፣ ዲክላራሲዮን፣ የማጓጓዣ ሰነድ እና የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ምዝገባ በማድረግ ታርጋ በማውጣት የሚፈጸም ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን የ16 ዓመት ቅጣት እንደተወሰነባቸው አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በክርክር ላይ ከነበሩ 1019 መዛግብት መካከል ምስክር ባለመቅረቡ 20 መዛግብት፣ ተከሳሽ ባለመቅረቡ ደግሞ 60 በድምሩ 80 መዛግብት እንደተቋረጡ ገልጸው በተለይ ተከሳሽ ባለመቅረብ እየተቋረጡ ያሉ መዛግብት ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ይህም ፍርድ ቤቱ ከመጥሪያ አያያዝ ጋር በደረሰበት ድምዳሜ ምክንያት በመሆኑ አሰራሩን ለመለወጥ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል፡፡